አማርኛ

እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል

ጃንዋሪ 11, 2020
ከጌታ መገለጥ በዓል በኋላ ያለው ቅዳሜ
የዛሬ ንባባት

“እርሱ ሊልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል።” ዮሐንስ 3:30

እነዚህ ኃይለኛና ትንቢታዊ የሆኑት የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ቃላት በየቀኑ በልባችን ሊያስተጋቡ ይገባል። ለመላው ማንነታችንና ልንሆን ለሚገባን ሰው አቅጣጫ ለመስጠት ይረዱናል። እነዚህ ቃላት ምን ማለት ናቸው? ዮሐንስ እዚህ ላይ ሁለት ነገሮችን እንደሚናገር ግልጽ ነው፦ 1) ኢየሱስ ሊልቅ ይገባል፣ 2) እኛ ልናንስ ይገባል።

በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ በሕይወታችን እየላቀ መሄዱ ሊኖረን የሚገባው ዋነኛ ግብ ነው። ይህ በትክክል ምን ማለት ነው? አእምሯችንንና ፈቃዳችንን ይበልጥ የራሱ ያደርጋል ማለት ነው። እኛ የእርሱ፣ እርሱም የእኛ ይሆናል ማለት ነው። በሕይወታችን ከሁሉ የሚቀድመው ግባችንና ምኞታችን በሁሉም ነገር ቅዱስ ፈቃዱ እንዲፈጸም መሆኑ ነው። ፍርሃት ወደ ጎን ተገፍቶ፣ ፍቅር የመኖራችን ምክንያት ይሆናል ማለት ነው። ጌታ በሕይወታችን እንዲልቅ መፍቀድ እጅግ ነፃ ያወጣናል። ከእንግዲህ ወዲህ ሁሉን በራሳችን ለማስተዳደር መጣር ስለማይኖርብን ነፃ ያወጣናል። አሁን ኢየሱስ በእኛ ውስጥና በእኛ በኩል ይኖራል።

ሁለተኛ፣ ዮሐንስ ማነስ እንዳለበት ሲናገር፣ ኢየሱስ እየተረከበ ሲሄድ የራሱ ፈቃድ፣ ምኞቶች፣ የላቀ ደረጃ ለመድረስ ያሉት ፍላጎቶች፣ ተስፋዎች ወዘተ መሟሟት አለባቸው ማለቱ ነው። ማንኛውም ራስ ወዳድነት መተው እንዳለበትና ለራስ ብቻ ሳይኖሩ መኖር የሕይወታችን መሠረታዊ መርሕ መሆን እንዳለበት ያመለክታል። በእግዚአብሔር ፊት “ማነስ” ማለት ትሑት መሆን ነው። ትሕትና ከእግዚአብሔር ያልሆነውን ሁሉ የመተውና እግዚአብሔር ብቻ በእኛ በኩል እንዲያበራ የመፍቀድ መንገድ ነው።

ዛሬ በዚህ ውብ የቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ አባባል ላይ አሰላስል። ጸሎትህ አድርገውና ደጋግመህ ተናገረው። ሕይወትህን የሚመራ መርሕ እንዲሆን ፍቀድለት።

ጌታ ሆይ፣ አንተ ልትልቅ፣ እኔ ግን ላንስ ይገባል። እባክህ ናና ነፍሴን ሙሉ በሙሉ የራስህ አድርጋት። አእምሮዬንና ልቤን ለውጥ፤ ፈቃዴን፣ ስሜቶቼንና ምኞቶቼን ምራ። የመለኮታዊ ሕይወትህ ቅዱስ መሣሪያ እንድሆንም አድርገኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት