አማርኛ

አስደናቂ እምነት

ፌብሩዋሪ 4፣ 2020
በዓመቱ መደበኛ ዘመን የአራተኛው ሳምንት ማክሰኞ
የዛሬ ንባባት

«ልብሱን ብቻ ብነካ እፈወሳለሁ።» ወዲያውም የደሟ ፍሰት ቆመ። ከሕመሟ እንደተፈወሰችም በሰውነቷ ተሰማት። ማርቆስ 5:28-29

ለአሥራ ሁለት ዓመታት በደም መፍሰስ ብዙ የተሠቃየችው ሴት ያሰበችውና ያጋጠማት ይህ ነበር። ብዙ ሐኪሞችን ፈልጋ በመሄድ፣ ለመፈወስ ባደረገችው ጥረት ያላትን ሁሉ አውጥታ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ምንም አልጠቀማትም።

እምነቷን ሁሉም እንዲያዩት የምትገልጥበትን ይህን ልዩ አጋጣሚ እንድታገኝ፣ እግዚአብሔር ሥቃይዋ ለእነዚያ ሁሉ ዓመታት እንዲቀጥል ፈቅዶ ሊሆን ይችላል። ይህ ክፍል ወደ ኢየሱስ ስትቀርብ በውስጧ ያሰበችውን መግለጡ ትኩረት የሚስብ ነው። «ልብሱን ብቻ ብነካ…» ይህ የውስጥ ሐሳቧ ውብ የእምነት ምሳሌ ነው።

እንደምትፈወስ እንዴት ልታውቅ ቻለች? ይህን እንዲህ ባለ ግልጽነትና ጽኑ እምነት እንድታምን ያደረጋት ምን ነበር? ለአሥራ ሁለት ዓመታት ልታገኘው ወደምትችለው ሐኪም ሁሉ ስትሄድ ከቆየች በኋላ፣ ለመፈወስ የሚያስፈልጋት የኢየሱስን ልብስ መንካት ብቻ መሆኑን ለምን በድንገት ተረዳች? መልሱ ቀላል ነው። የእምነት ስጦታ ስለተሰጣት ነው።

ይህ የእምነቷ ምሳሌ፣ እምነት እግዚአብሔር ብቻ ሊገልጠው የሚችለውን ነገር ከተፈጥሮ በላይ በሆነ መንገድ ማወቅ መሆኑን ያሳያል። በሌላ አነጋገር፣ እንደምትፈወስ ታውቅ ነበር፤ ይህን ፈውስ የሚመለከተው እውቀቷም ከእግዚአብሔር እንደተሰጣት ስጦታ ደረሳት። አንዴ ይህ እውቀት ከተሰጣት በኋላ፣ በእርሱ መሠረት እርምጃ መውሰድ ነበረባት፤ እንዲህ በማድረጓም ታሪኳን ለሚያነቡ ሁሉ አስደናቂ ምስክርነት ሰጠች።

ሕይወቷ፣ በተለይም ይህ ያጋጠማት ነገር፣ እኛም ለማዳመጥ ፈቃደኞች ከሆንን እግዚአብሔር ጥልቅ እውነቶችን እንደሚነግረን ለመገንዘብ ሁላችንንም ሊያነሳሳን ይገባል። እርሱ ያለማቋረጥ ይናገረናል፣ የፍቅሩንም ጥልቀት ይገልጥልናል፤ እምነት በግልጽ ወደሚታይበት ሕይወት እንድንገባም ይጠራናል። እምነታችን የሕይወታችን መሠረት ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎችም ኃይለኛ ምስክርነት እንዲሆን ይፈልጋል።

ዛሬ፣ ይህች ሴት በውስጧ ስለነበራት ጽኑ እምነት አሰላስል። እግዚአብሔር ሲናገራት ለመስማት ራሷን ክፍት ስላደረገች፣ እርሱ እንደሚፈውሳት ታውቅ ነበር። አንተም በውስጥህ ለእግዚአብሔር ድምፅ ምን ያህል ትኩረት እንደምትሰጥ አሰላስል፤ ይህች ቅድስት ሴት የመሰከረችውን የእምነት ጥልቀት ለመቀበልም ልብህን ለመክፈት ሞክር።

ጌታ ሆይ፣ እወድሃለሁ፤ አንተን ማወቅና በየዕለቱ ስትናገረኝ መስማት እመኛለሁ። አንተንና ለሕይወቴ ያለህን ፈቃድ ማወቅ እንድችል እባክህ እምነቴን ጨምርልኝ። ለሌሎች የእምነት ምስክር እሆን ዘንድ፣ እባክህ እንደ ፈቃድህ ተጠቀምብኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት