አማርኛ

ሐቀኝነትና ቅንነት

ፌብሩወሪ 16፣ 2020
በዓመቱ ውስጥ ያለው ስድስተኛ እሑድ፣ ዓመት ሀ
የዛሬ ንባቦች

«አዎ» ስትሉ «አዎ»፣ «አይ» ስትሉም «አይ» ይሁን። ከዚህ የሚበልጠው ሁሉ ከክፉው ነው።  ማቴ. 5:37

ይህ የጌታችን ትምህርት፣ ጌታችን ስለ ጥንቶቹ ትእዛዛት ተከታታይ አዳዲስና ጥልቅ ትምህርቶችን ከሰጠ በኋላ የመጣ ነው።  ኢየሱስ መግደል፣ ማመንዘር ወይም መዋሸት እንደሌለብን የሚናገሩትን የብሉይ ኪዳን ትምህርቶች ይጠቅሳል።  ከዚያም እያንዳንዱን ትእዛዝ የበለጠ ጥልቅ በሆነ ማስተዋል ያብራራል።  በኢየሱስ ትምህርት አዲስ ሕግ ውስጥ፣ «አትግደል» የሚለው ትእዛዝ በልባችን ያለውን ቁጣ ሁሉ ማስወገድ እንዳለብን የሚያስተምር ጥልቅ ትርጉም ይሰጠዋል።  «አታመንዝር» የሚለውም በልባችን ውስጥ ሥጋዊ ምኞት ሊኖር እንደማይገባ የሚያስተምር ጥልቅ ትርጉም ይሰጠዋል።  «አትዋሽ» የሚለውም ከላይ በተጠቀሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ጥልቅ ትርጉም ተሰጥቶት በአዲስ መንገድ ቀርቧል።

በመጀመሪያ ልብ ማለት ያለብን፣ የኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ወደ አዲስና ጥልቅ የሥነ ምግባር ደረጃ እንደሚያደርሱን የሚያሳየውን አጠቃላይ እውነታ ነው።  ከእንግዲህ ወዲህ ከባድ ኃጢአት የሆኑ ድርጊቶችን ከመፈጸም መቆጠብ ብቻ አይደለም የሚጠበቅብን፤ አሁን ወደ እነዚህ ድርጊቶች የሚያዘነብሉንን ውስጣዊ ዝንባሌዎች እንኳን እንድናስወግድ ተጠርተናል።  ውጫዊ ድርጊቶቻችንን ብቻ ሳይሆን፣ ልባችንንም ማንጻት አለብን።

«አዎ» ስንል «አዎ»፣ «አይ» ስንልም «አይ» መሆን አለበት የሚለው ይህ ክፍል፣ የምንናገራቸው ቃላት ከልባችን ሐቀኝነትና ቅንነት መፍለቅ እንዳለባቸው ኢየሱስ የሚያስተምርበት መንገድ ነው።  በሌላ አነጋገር፣ በአንደበታችን የምንናገረው ከውስጣችን ጥልቀት መነገር አለበት።  ቃላችን በልባችን ካለው መፍለቅ አለበት።

ይህ ለእኛ እንዴት ያለ ጥልቅ ትምህርት ነው!  በሕይወት ውስጥ ባለ ሁለት ፊት ሆኖ መኖር በጣም ቀላል ነው።  ከሁሉ ይበልጥ ይጠቅመናል፣ በጎ ሰዎች አስመስሎ ያሳየናል፣ ወይም አንድን ሁኔታ ቀላል ያደርግልናል ብለን የምናስበውን ብቻ መናገር ቀላል ነው።  ሌሎች መስማት ይፈልጋሉ ብለን የምናስበውን መናገር፣ ወይም ሕይወታችንን እጅግ በጎ አስመስሎ የሚያቀርብ ነገር መናገር፣ የተለመደ ዝንባሌ ነው። 

እውነተኛ ሐቀኝነትና ቅንነት፣ በልባችን ውስጥ ካለው እውነት ብቻ ተነሥተን እንድንናገር ይጠይቃሉ።  አይ፣ በልባችን ያለውን እውነት ሁሉ በአደባባይ የመግለጥ የሥነ ምግባር ግዴታ የለብንም።  አንዳንድ ነገሮች ለእግዚአብሔር ብቻ ወይም በኑዛዜ ለመግለጥ መጠበቅ አለባቸው።  ነገር ግን መናገር እንዳለብን ሲሰማን፣ ቃላችን በሁሉም ረገድ ለእውነት የታመነ መሆኑ አስፈላጊ ነው።  ያለበለዚያ ቃላችን ትርጉም የሌለው፣ አሳሳችና በመጨረሻም አጥፊ ይሆናል።

ዛሬ ስለ ራስህ ሐቀኝነትና ቅንነት አሰላስል።  ለሌሎች ስትናገር፣ ቃላትህ በልብህ ውስጥ ሕያው ከሆነው እውነት ይፈልቃሉን?  እግዚአብሔር ቃላትህን ሲሰማ ሐቀኝነትን ያይባቸዋልን?  ከውይይት በኋላ ወደ ጸሎት ተመልሰህ፣ በሰላምና በንጹሕ ሕሊና በጌታህ ፊት መቅረብ ትችላለህን?  ሐቀኛ ለመሆን የምትታገል ከሆነ፣ ቅንነትን የሚያፈራው ሐቀኝነት መሆኑን እወቅ።  በሕይወትህ የቅንነትን በጎነት ፈልግ፤ ጌታችንም ከልቡ የሚናገር የእውነት ሰው በመሆን ይህን እንድታገኝ ይረዳሃል።

ጌታ ሆይ፣ እባክህ ልቤን ንጹሕ አድርግልኝ።  ሐቀኛና ቅን ሰው እንድሆን እርዳኝ።  በልቤ የምታኖረው እውነት ለድርጊቶቼና ለቃላቶቼ መሠረት ይሁን።  ዘወትር እንድናገር የምትሰጠኝን እየተናገርሁ፣ በንጹሕ ሕሊና ልናገር።  ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት