መጋቢት 13፣ 2020
በጾመ አርባ ሁለተኛ ሳምንት ዓርብ
የዛሬ ንባባት

ግንበኞች የናቁት ድንጋይ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ። ማቴዎስ 21:42
በዘመናት ሁሉ ከደረሱት የመገፋት ሁኔታዎች መካከል ከሁሉ ጎልቶ የሚታይ አንድ አለ። ይህም የእግዚአብሔር ልጅ መገፋት ነው። በኢየሱስ ልብ ውስጥ ከንጹሕና ፍጹም ፍቅር በስተቀር ሌላ ምንም አልነበረም። ለሚያገኘው ሰው ሁሉ ከሁሉ የተሻለውን ይመኝ ነበር። የሕይወቱንም ስጦታ ለሚቀበለው ሁሉ ለመስጠት ፈቃደኛ ነበር። ብዙዎች ይህን ስጦታ ቢቀበሉም፣ ብዙዎችም አልተቀበሉትም።
ኢየሱስ የደረሰበት መገፋት ጥልቅ ሕመምና ሥቃይ እንዳስከተለበት መረዳት አስፈላጊ ነው። በእርግጥ መሰቀሉ እጅግ አሠቃይ ነበር። ነገር ግን ብዙዎች እሱን ባለመቀበላቸው በልቡ የደረሰበት ቁስል ከሁሉ የበለጠው ሕመሙ ነበር፤ ከሁሉ የከፋውንም ሥቃይ አስከትሎበታል።
በዚህ መልኩ መሠቃየቱ የፍቅር እንጂ የድክመት ተግባር አልነበረም። ኢየሱስ በውስጡ የተሠቃየው ከትዕቢት ወይም ለራሱ ካለው ዝቅተኛ ግምት የተነሣ አልነበረም። ይልቁንም ልቡ የታመመው እጅግ በጥልቅ ስለወደደ ነበር። ያም ፍቅር ተቀባይነት ባጣ ጊዜ፣ በብፁዓን ትምህርቶች ውስጥ በተጠቀሰው ቅዱስ ኀዘን ሞላው፤ «የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው…» (ማቴዎስ 5:4)። ይህ ዓይነቱ ኀዘን ተስፋ መቁረጥ አልነበረም፤ ይልቁንም የሌላውን ፍቅር ማጣት በጥልቅ የተሰማበት ሁኔታ ነበር። ቅዱስ ነበር፤ ለሁሉም ካለው የሚነድድ ፍቅርም የመነጨ ነበር።
መገፋት ሲደርስብን፣ የሚሰማንን ሕመም ለይተን መረዳት አስቸጋሪ ነው። የሚሰማንን የልብ ቁስልና ቁጣ፣ የምናዝንላቸውን ሰዎች ይበልጥ በጥልቅ እንድንወድ ወደሚያነሣሣን «ቅዱስ ኀዘን» እንዲለወጥ ማድረግ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ይህን ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ጌታችን ያደረገው ይህንኑ ነው። ኢየሱስ ይህን ማድረጉ ያስገኘው ፍሬ የዓለም ድኅነት ነበር። ኢየሱስ ዝም ብሎ ተስፋ ቆርጦ ቢተው ኖሮ ምን እንደሚሆን አስቡ። ኢየሱስ በተያዘበት ጊዜ፣ እልፍ አእላፍ መላእክት መጥተው እንዲያድኑት ቢጠራቸው ኖሮስ? «እነዚህ ሰዎች ይህን ሁሉ የሚደረግላቸው አይደሉም!» ብሎ በማሰብ ይህን ቢያደርግ ኖሮስ? ውጤቱ፣ በሞቱና በትንሣኤው የተገኘውን ዘላለማዊ የድኅነት ስጦታ ፈጽሞ አለማግኘታችን ይሆን ነበር። ሥቃይም ወደ ፍቅር ባልተለወጠ ነበር።
መገፋት ክፋትን ለመዋጋት ካሉን እጅግ ታላላቅ ስጦታዎች አንዱ ሊሆን ይችላል፤ ዛሬ በዚህ ጥልቅ እውነት ላይ አሰላስሉ። ከታላላቅ ስጦታዎች አንዱ «ሊሆን ይችላል» የምንለው፣ ሁሉም ነገር በመጨረሻ በምንሰጠው ምላሽ ላይ ስለሚመሠረት ነው። ኢየሱስ፣ «አባት ሆይ፣ ይቅር በላቸው፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና» ብሎ በጮኸ ጊዜ፣ በፍጹም ፍቅር ምላሽ ሰጠ። ከሁሉ የከፋው መገፋት በደረሰበት ጊዜ ያሳየው ይህ የፍጹም ፍቅር ተግባር፣ የቤተ ክርስቲያን «የማዕዘን ራስ ድንጋይ»፣ በዚህም የአዲስ ሕይወት የማዕዘን ራስ ድንጋይ እንዲሆን አስቻለው! ይህን ፍቅር እንድንመስል፣ ይቅር በማለት ብቻ ሳይሆን ቅዱሱን የምሕረት ፍቅር በመስጠትም የእሱ ችሎታ ተካፋዮች እንድንሆን ተጠርተናል። ይህን ስናደርግ፣ እኛም ፍቅርና ጸጋን እጅግ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች የፍቅርና የጸጋ የማዕዘን ራስ ድንጋይ እንሆናለን።
ጌታ ሆይ፣ ያ የማዕዘን ራስ ድንጋይ እንድሆን እርዳኝ። በተጎዳሁ ቁጥር ይቅር እንድል ብቻ ሳይሆን፣ በምላሹም ፍቅርና ምሕረት እንድሰጥ እርዳኝ። የዚህ ፍቅር መለኮታዊና ፍጹም አርአያ አንተ ነህ። «አባት ሆይ፣ ይቅር በላቸው፤ የሚያደርጉትን አያውቁምና» ብዬ ከአንተ ጋር በመጮኽ፣ የዚሁ ፍቅር ተካፋይ ልሁን። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
40 ቀናት ከመስቀሉ ሥር – ስድስተኛው ከአሥር ማሰላሰያ – ከተአምራት ሁሉ የሚበልጠው




