ጁን 25፣ 2020
በዓመቱ ተራ ጊዜ የአሥራ ሁለተኛው ሳምንት ሐሙስ
የዛሬ ንባቦች

“እነዚህን ቃሎቼን የሚሰማና በእነርሱ የሚሠራ ሁሉ፣ ቤቱን በዐለት ላይ የሠራ አስተዋይ ሰውን ይመስላል። ዝናብ ዘነበ፣ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰና ያንን ቤት መታው። ነገር ግን በዐለት ላይ በጽኑ ተመሥርቶ ስለነበር አልፈረሰም።” ማቴዎስ 7:24-25
ከዚህ ከላይ ካለው ክፍል ቀጥሎ፣ ቤቱን በአሸዋ ላይ የሠራ ሰው በተቃራኒ ምሳሌነት ይቀርባል። ነፋስና ዝናብ መጡ፣ ቤቱም ፈረሰ። ይህ ግልጽ ንጽጽር፣ ቤትን በጠንካራ ዐለት ላይ መሥራት እጅግ የተሻለ መሆኑን ማንም ሰው እንዲገነዘብ ያደርገዋል።
ቤቱ የአንተ ሕይወት ነው። ይህም የሚያስነሣው ጥያቄ በቀላሉ፣ ምን ያህል ጠንካራ ነኝ? የሚል ነው። በሕይወቴ የሚያጋጥሙኝን አውሎ ነፋሶች፣ መከራዎችና መስቀሎች ለመጋፈጥ ምን ያህል ጠንካራ ነኝ?
ሕይወት ቀላል ሲሆንና ሁሉም ነገር ያለ ችግር ሲሄድ፣ ሁልጊዜ ታላቅ ውስጣዊ ጥንካሬ አያስፈልገንም። ገንዘብ በብዛት ሲኖረን፣ ብዙ ወዳጆች ሲኖሩን፣ ጤናችን ጥሩ ሲሆንና ቤተሰባችን ሁሉ ተስማምቶ ሲኖር፣ ሕይወት ጥሩ ሊሆን ይችላል። በዚህ ሁኔታ ሕይወት ቀላልም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንዳች አውሎ ነፋስ ሳይገጥማቸው በሕይወት መጓዝ የሚችሉ ጥቂቶች ናቸው። ይህ ሲከሰት፣ ውስጣዊ ጥንካሬያችን ይፈተናል፤ በውስጣችን ያሉትም ጽኑ እምነቶች የሚሰጡን ብርታት ያስፈልገናል።
ኢየሱስ በተናገረው በዚህ ታሪክ፣ ቤቱን የመቱት ዝናብ፣ ጎርፍና ነፋስ በእርግጥ መልካም ነገር ናቸው። ለምን? ምክንያቱም የቤቱ መሠረት ጥንካሬውን እንዲያሳይ ዕድል ይሰጡታል። በእኛም ሕይወት እንዲሁ ነው። የሕይወታችን መሠረት ለእግዚአብሔር ቃል ያለን ታማኝነት መሆን አለበት። በእግዚአብሔር ቃል ታምናለህ? አሰላስለኸዋል፣ አጥንተኸዋል፣ በልብህ አኑረኸዋል? የእግዚአብሔር ቃል የሕይወትህ መሠረት እንዲሆን ፈቅደሃል? ኢየሱስ፣ ጠንካራ መሠረት የሚኖረን ቃሎቹን ሰምተን በእነርሱ ስንሠራ ብቻ መሆኑን በግልጽ ይናገራል።
ዛሬ፣ ኢየሱስ የሚናገረውን ሁሉ ምን ያህል በጥልቅ እንደምታምን አሰላስል። በተናገረው በእያንዳንዱ ቃል ትታመናለህ? በሕይወት ከሚያጋጥሙህ ሁሉ በላቁ ፈተናዎች መካከል እንኳ፣ በተስፋ ቃሎቹ ለመደገፍ የሚያበቃ እምነት በእርሱ አለህ? እርግጠኛ ካልሆንክ፣ ቃሉን በጸሎት ለማንበብ ዳግመኛ ቁርጠኝነትህን የምታድስበት መልካም ቀን ዛሬ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ሁሉ እውነት ነው፤ ለቀረው ሕይወታችን ጽኑ መሠረት ለመገንባት የሚያስፈልጉንም እነዚህ እውነቶች ናቸው።
ጌታ ሆይ፣ ቃሎችህን እንድሰማና በእነርሱ እንድሠራ እርዳኝ። የሕይወት አውሎ ነፋሶች እጅግ ኃይለኛ በሚመስሉበት ጊዜ እንኳ፣ በተስፋ ቃሎችህ እንዳምንና በአንተ እንድታመን እርዳኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።





