ኦገስት 8፣ 2020
በዓመቱ መደበኛ ዘመን የአሥራ ስምንተኛው ሳምንት ቅዳሜ
የዛሬ ንባቦች

አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ ቀርቦ በፊቱ ተንበረከከና፣ “ጌታ ሆይ፣ ልጄን ማረው፤ እብድ ነውና እጅግ ይሠቃያል፤ ብዙ ጊዜ በእሳት፣ ብዙ ጊዜም በውኃ ውስጥ ይወድቃል። ወደ ደቀ መዛሙርትህ አመጣሁት፣ ግን ሊፈውሱት አልቻሉም” አለ። ማቴዎስ 17:14-16
እንግዲህ፣ ይህ ጸሎት ምናልባት የብዙ ወላጆችን ጸሎት ይመስላል። ብዙ ወጣቶች በችግርና በኃጢአት ውስጥ ከመውደቅ አንጻር “በእሳት” ወይም “በውኃ ውስጥ” ሊወድቁ ይችላሉ። ብዙ ወላጆችም በመጨረሻ ተንበርክከው እግዚአብሔርን እርዳታ ይለምናሉ።
ይህ መልካምና ከልብ የሆነ ጸሎት ነው። በዛሬው ጊዜ “እብድ” የሚለውን ቃል ከስድብ ውጭ ብዙውን ጊዜ ባንጠቀምበትም፣ በዚህ ክፍል ውስጥ ይህ ቃል ሰውየው ልጁ በሆነ ዓይነት የሥነ ልቡናና የመንፈስ ሕመም እየተሠቃየ መሆኑን እንደሚያምን የሚገልጽ ሊሆን ይገባል። በእርግጥም፣ ክፍሉ በመቀጠል ኢየሱስ ከልጁ ውስጥ ጋኔን እንዳወጣ ይገልጻል። ይህ የጋኔን መንፈሳዊ ጭቆና ከባድ የሥነ ልቡና ችግሮችንም አስከትሎ ነበር።
በዚህ ክፍል ውስጥ የሚገኘው የመጀመሪያው መልካም ዜና፣ አባትየው ለልጁ ያስብ እንደነበርና በእርሱ ላይ ተስፋ እንዳልቆረጠ ነው። ምናልባት አባትየው በቁጣ፣ በልብ ስብራት ወይም በብስጭት ተነሣሥቶ ልጁን መካድ ቀላል ይሆንለት ነበር። ልጁን ምንም የማይረባና ከዚያ በኋላ ትኩረቱን የማይገባው ሰው አድርጎ መቁጠር ቀላል ይሆንለት ነበር። ሆኖም የሆነው ይህ አልነበረም።
ሰውየው ወደ ኢየሱስ መምጣት ብቻ ሳይሆን፣ “ርኅራኄ” እየለመነ በኢየሱስ ፊት ተንበረከከ። ርኅራኄ ማለት ምሕረትንና አዘኔታን በሌላ ቃል መግለጽ ነው። ለልጁ ተስፋ እንዳለና ያም ተስፋ በኢየሱስ ምሕረትና ርኅራኄ ውስጥ እንደሚገኝ ያውቅ ነበር።
ይህ ክፍል እርስ በርሳችን መጸለይ እንዳለብን የሚያሳየውን ቀላል እውነት ይገልጥልናል። በተለይም ለእኛ ቅርብ ለሆኑና ከሁሉ ይልቅ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው መጸለይ አለብን። ተስፋ የሌለው ሰው የለም። በጸሎትና በእምነት ሁሉ ይቻላል።
ዛሬ፣ በሕይወትህ ውስጥ ተስፋ መቁረጥ የጀመርህበት ሰው እንዳለ አስብ። ምናልባት የምትችለውን ሁሉ ሞክረህ ይሆናል፣ ሰውየው ግን ወደ እግዚአብሔር ከሚወስደው መንገድ መራቁን ቀጥሎ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ፣ ጥሪህ ለዚያ ሰው መጸለይ መሆኑን እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። የተጠራኸው በቸልታና በችኮላ ብቻ እንድትጸልይ አይደለም፤ ይልቁንም ለዚያ ሰው ጥልቅና በእምነት የተሞላ ጸሎት እንድታቀርብ ነው። ኢየሱስ ለሁሉ መልስ እንደሆነና ሁሉንም ማድረግ እንደሚችል እወቅ። ዛሬ፣ ነገና በየዕለቱ ያንን ሰው ለእግዚአብሔር ምሕረት አደራ ስጥ። ተስፋ አትቁረጥ፤ ይልቁንም እግዚአብሔር ፈውስንና የሕይወት ለውጥን ማምጣት እንደሚችል ተስፋህን ጠብቅ።
ጌታ ሆይ፣ እባክህ ለእኔ፣ ለቤተሰቤና ለተቸገሩ ሁሉ ርኅራኄ አድርግ። ዛሬ በተለይ ለ(_____) እጸልያለሁ። ፈውስን፣ ቅድስናንና የሕይወት ለውጥን አምጣ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
የዕለቱ ቅዱስ – ቅዱስ ዶሚኒክ፣ ካህን
ምስል፦ ኢየሱስ የአንድ መኮንን ልጅ ሲፈውስ፤ በዦዜፍ-ማሪ ቪየን የተሣለ




