ኖቬምበር 16፣ 2020
በዓመቱ ውስጥ ያለው መደበኛ ጊዜ ሠላሳ ሦስተኛ ሳምንት ሰኞ
የዛሬ ንባባት
ታላቋ ቅድስት ገርትሩድ፣ ድንግል—አማራጭ መታሰቢያ

እርሱ ግን፣ «የዳዊት ልጅ ሆይ፣ ማረኝ!» እያለ ከዚያም ይበልጥ ይጮኽ ነበር። ሉቃስ 18:39c
መልካም አደረገ! ይህ ሰው ብዙዎች ክፉ አድርገው የሚያስተናግዱት ዓይነ ስውር ለማኝ ነበር። ምንም የማይረባና ኃጢአተኛ እንደሆነ ሰው ይቆጥሩት ነበር። ኢየሱስ እንዲምረው መጮኽ ሲጀምር፣ በዙሪያው የነበሩት ሰዎች ዝም እንዲል ነገሩት። ዓይነ ስውሩ ግን ምን አደረገ? ለጭቆናቸውና ለፌዛቸው እጅ ሰጠን? ፈጽሞ አልሰጠም። ይልቁንም፣ «ከዚያም ይበልጥ ይጮኽ ነበር!» ኢየሱስም እምነቱን ተመልክቶ ፈወሰው።
ከዚህ ሰው ሕይወት ሁላችንም የምንማረው ታላቅ ትምህርት አለ። በሕይወታችን ውስጥ የሚያደቁን፣ የሚያስከፉንና ተስፋ እንድንቆርጥ የሚፈትኑን ብዙ ነገሮች ያጋጥሙናል። የሚጫኑንና ለመቋቋም የሚከብዱን ብዙ ነገሮች አሉ። ታዲያ ምን ማድረግ አለብን? ለትግሉ እጅ ሰጥተን፣ በራሳችን ላይ እያዘንን ወደ ብቸኝነት ጉድጓድ ማፈግፈግ አለብን?
ይህ ዓይነ ስውር ሰው ምን ማድረግ እንዳለብን ፍጹም ምስክርነት ይሰጠናል። ጭቆና፣ ድብርት፣ ብስጭት ሲሰማን፣ ሌሎች እንዳልተረዱን ሲሰማን ወይም እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን፣ ምሕረቱን እየለመንን ከዚያም በላቀ ጉጉትና ድፍረት ወደ ኢየሱስ ለመዞር ይህን እንደ አጋጣሚ ልንጠቀምበት ይገባናል።
የሕይወት ችግሮች ከሁለት ውጤቶች አንዱን ሊያመጡብን ይችላሉ። ወይ ያደቁናል፣ ወይም የበለጠ ያጠነክሩናል። የሚያጠነክሩንም በነፍሳችን ውስጥ በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ያለንን መታመንና መደገፍ የበለጠ እንዲያድግ በማድረግ ነው።
ዛሬ፣ ከሁሉ ይልቅ ለመደበት ስለሚፈትንህ ነገር አሰላስል። የሚጫንህና ለመቋቋም የሚከብድህ ምንድን ነው? ይህን ትግል ከዚያም በላቀ ጉጉትና ቅንዓት የእግዚአብሔርን ምሕረትና ጸጋ ለመለመን እንደ አጋጣሚ ተጠቀምበት።
ጌታ ሆይ፣ በድካሜና በትግሌ ውስጥ ከዚያም በላቀ ጉጉት ወደ አንተ እንድዞር እርዳኝ። በሕይወቴ ውስጥ በጭንቀትና በብስጭት ጊዜ ከዚያም ይበልጥ በአንተ እንድደገፍ እርዳኝ። የዚህ ዓለም ክፋትና ጭካኔ በሁሉም ነገር ወደ አንተ ለመዞር ያለኝን ቁርጠኝነት ከማጠናከር በቀር ሌላ ነገር አያድርግብኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
የዕለቱ ቅዱሳን –የስኮትላንዷ ቅድስት ማርጋሬት እንዲሁም ታላቋ ቅድስት ገርትሩድ፣ ድንግል
ከላይ የሚታየው ዋና ምስል፦ «የዓይነ ስውሩ መፈወስ» የተሰኘው ሥዕል በትክክል የተገለበጠ ቅጂ። ሠዓሊው ካርል ብሎክ ነው።




