አማርኛ

ለሌሎች አድርጉ…

ጁን 21, 2022
በዓመቱ ተራ ዘመን የአሥራ ሁለተኛው ሳምንት ማክሰኞ
የዛሬ ንባቦች

ቅዱስ አሎይሲየስ ጎንዛጋ፣ መነኩሴ—መታሰቢያ

ቪዲዮ

“ሌሎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም ለእነርሱ አድርጉ። ሕጉና ነቢያቱ ይህ ነው።” ማቴዎስ 7:12

ይህ የለመድነው አባባል በብሉይ ኪዳን የተደነገገ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነበር። በሕይወታችን የምንመራበት ጥሩ ተግባራዊ መመሪያ ነው።

ሌሎች “ምን እንዲያደርጉልህ” ትፈልጋለህ? በዚህ ላይ አስብ፤ ለራስህም እውነተኛ ለመሆን ሞክር። ለራሳችን እውነተኞች ከሆንን፣ ሌሎች ብዙ ነገር እንዲያደርጉልን እንደምንፈልግ ማመን አለብን። እንዲያከብሩን፣ ክብራችንን ጠብቀው እንዲይዙን፣ በፍትሕ እንዲያስተናግዱን ወዘተ እንፈልጋለን። ከዚህም በበለጠ ጥልቅ ደረጃ፣ እንዲወዱን፣ እንዲረዱን፣ እንዲያውቁንና እንዲንከባከቡን እንፈልጋለን።

በውስጣችን ያለውን፣ ከሌሎች ጋር በፍቅር ግንኙነት ለመኖርና በእግዚአብሔር ለመወደድ እግዚአብሔር የሰጠንን ተፈጥሯዊ ናፍቆት ሁላችንም ለማወቅ መጣር አለብን። ይህ ምኞት ሰው መሆን ከሚያመለክተው መሠረታዊ እውነታ ጋር ይያያዛል። እኛ ሰዎች የተፈጠርነው ለዚያ ፍቅር ነው። ከላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፣ ለመቀበል የምንመኘውን ለሌሎች ለመስጠት ዝግጁዎችና ፈቃደኞች መሆን እንዳለብን ያሳያል። በውስጣችን ያለውን ፍቅር የማግኘት ተፈጥሯዊ ምኞት ማወቅ ከቻልን፣ ለመውደድ ያለንንም ምኞት ለማሳደግ መጣር አለብን። ለራሳችን ፍቅርን በምንፈልግበት መጠን፣ ሌሎችን የመውደድ ምኞታችንንም ማሳደግ አለብን።

ይህ ከሚመስለው በላይ ከባድ ነው። ራስ ወዳድ ዝንባሌያችን፣ ከሌሎች ፍቅርና ምሕረትን እንድንጠይቅና እንድንጠብቅ ያደርገናል፤ በተመሳሳይ ጊዜ ግን እኛ ምን ያህል እንደምንሰጥ ሲሆን፣ ለራሳችን እጅግ ዝቅ ያለ መስፈርት እናስቀምጣለን። ቁልፉ በመጀመሪያ ትኩረታችንን በግዴታችን ላይ ማድረግ ነው። ምን ለማድረግና እንዴት ለመውደድ እንደተጠራን ለማየት መጣር አለብን። ይህን እንደ ቀዳሚ ግዴታችን ስንመለከተውና በተግባር ለመኖር ስንጥር፣ ለመቀበል ከመፈለግ ይልቅ በመስጠት እጅግ የበለጠ እርካታ እንደምናገኝ እንደርስበታለን። ሌሎች “ለእኛ ምን እንደሚያደርጉ” ሳንመለከት፣ “እኛ ለሌሎች ማድረጋችን” በእውነት ውስጣዊ እርካታ የምናገኝበት መሆኑን እናያለን።

ዛሬ፣ ሌሎች እንዲወዱህና እንዲያከብሩህ በልብህ ባለው ተፈጥሯዊ ምኞት ላይ አሰላስል። ከዚያም በዙሪያህ ያሉትን ሰዎች በምትይዝበት መንገድ ይህን የትኩረትህ ማዕከል አድርገው።

የፍጹም ምኞቶች ጌታ ሆይ፣ ሌሎች እንዲያደርጉልኝ የምመኘውን እኔም ለእነሱ እንዳደርግ እርዳኝ።  በልቤ ያለው የፍቅር ጉጉት ሌሎችን ለመውደድ የሚያነሳሳኝ እንዲሆን እርዳኝ።  ራሴን ስሰጥ፣ በዚያ ስጦታ ሙላትና እርካታ እንዳገኝ እርዳኝ።  ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

አገር አቀፍ የቅዱስ ቁርባን መንፈሳዊ መታደስ
ጁን 19፣ 2022—በክርስቶስ ሥጋ ታላቅ በዓል ይጀምራል

ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ የሚቀርብ የዘጠኝ ቀን ጸሎት
የዘጠኝ ቀን ጸሎቱ ቀናት፦ ጁን 15-23, 2022
ጁን 24, 2022፦ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ታላቅ በዓል

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

ሁሉም ቅዱሳን/በዓላት

የዕለቱ ቅዱስ – ቅዱስ አሎይሲየስ ጎንዛጋ፣ መነኩሴ

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

 ከላይ የቀረበው ምስል፦ የጌታ ተለውጦ መታየት፣ በዱቾ ዲ ቡዎኒንሴኛ፣ ከዊኪሚዲያ ኮመንስ የተገኘ