ኤፕሪል 14, 2023
በፋሲካ ስምንት ቀናት በዓል ውስጥ ያለው ዓርብ
የዛሬ ንባቦች

ኢየሱስም፣ “ኑ፣ ቁርስ ብሉ” አላቸው። ከደቀ መዛሙርቱም ማንም፣ “አንተ ማን ነህ?” ብሎ ሊጠይቀው አልደፈረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና። ኢየሱስም መጥቶ እንጀራውን አነሣና ሰጣቸው፤ ዓሣውንም እንዲሁ አደረገ። ይህም ኢየሱስ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ የተገለጠበት ሦስተኛው ጊዜ ነበር። ዮሐንስ 21:12–14
ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ የተገለጠባቸው ጊዜያት በምሥጢር የተከበቡ ነበሩ። ይህም ግራ የሚያጋባ ምሥጢር ሳይሆን፣ እጅግ ጥልቅ የሆነና በአክብሮት የተሞላ ድንቅ ስሜትን የሚያሳድር ምሥጢር ነበር። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በተገለጠበት በዚህ ሦስተኛ ጊዜ፣ ሌሊቱን ሙሉ ምንም ሳያጠምዱ ካደሩ በኋላ፣ መጀመሪያ ከባሕሩ ዳርቻ ሆኖ ተናገራቸው። እንደገና እንዲሞክሩና መረቡን በጀልባው ቀኝ በኩል እንዲጥሉ ነገራቸው። የሚያናግራቸው ኢየሱስ መሆኑን እንኳን ሳያውቁ እንዳላቸው አደረጉ። ነገር ግን መጎተት ከሚችሉት በላይ ዓሣ ሲያጠምዱ፣ ጌታ መሆኑን አወቁ።
በዚህ የትንሣኤ መገለጥ ውስጥ ያለው “ምሥጢር” ብዙ ገጽታዎች አሉት። ደቀ መዛሙርቱ በመጀመሪያ ኢየሱስን ለምን አላወቁትም? ኢየሱስ መረቡን በጀልባው ቀኝ በኩል እንዲጥሉ ለምን አዘዛቸው? ኢየሱስ በዚህ መቶ ሃምሳ ሦስት ትላልቅ ዓሦችን ባጠመዱበት ክስተት ለምን ታወቀ? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በባሕሩ ዳርቻ ቁርስ ያዘጋጅ የነበረው ለምንድን ነው? ዮሐንስስ “ከደቀ መዛሙርቱ ማንም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ብሎ ሊጠይቀው አልደፈረም” ብሎ የጻፈው ለምንድን ነው? ለእነዚህ ምሥጢሮች ሁሉ በዘመናት ሂደት ቅዱሳንና ታላላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የሰጧቸው መልሶች ቢኖሩም፣ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ የተገለጠባቸው ጊዜያት በእርግጥም በምሥጢር የተከበቡ እንደነበሩ ብቻ ማሰላሰሉም ጠቃሚ ነው።
በምሥጢር ዙሪያ በተጻፈ ልቦለድ ውስጥ፣ አንባቢው ምሥጢሩን ለመረዳትና ለመፍታት እንዲሞክር የሚረዱት የተለያዩ ግልጽ ያልሆኑ ፍንጮች ይሰጡታል። ምሥጢሩን መፍታት ይበልጥ አስደሳችና አፈታታኝ እንዲሆን፣ ፍንጮቹ ሆን ተብሎ ግልጽ አይደረጉም። ሆኖም፣ ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ መገለጡን እንደከበበው የእምነት ምሥጢር ያለ “የእምነት ምሥጢር” ሲሆን፣ ምሥጢሩ ፈጽሞ ሌላ ዓይነት ነው። በእነዚህ ሁኔታዎች ምሥጢሩ ጥልቀትና ስፋት ያለው ሲሆን፣ ወሰን ወደሌለው የእግዚአብሔር ባሕርይና ወደ ማዳን ሥራው ይበልጥ እየጠለቅን እንድንገባ ሊስበን የሚችል ነው።
ለምሳሌ፣ ከላይ የተጠቀሰውን ይህን አንድ ዓረፍተ ነገር እንመልከት፦ “ከደቀ መዛሙርቱም ማንም፣ ‘አንተ ማን ነህ?’ ብሎ ሊጠይቀው አልደፈረም፤ ጌታ መሆኑን አውቀው ነበርና።” ኢየሱስ በባሕሩ ዳርቻ ቁርስ ሲያዘጋጅ፣ ደቀ መዛሙርቱ በዙሪያው ተሰብስበው፣ በአክብሮትና በአድናቆት ተሞልተው በዚያ ተቀምጠው የነበሩ ይመስላል። በዚህ መገለጡ በዝምታ ያሳዩት አክብሮትና አድናቆት፣ ቃላት በቂ እንዳልሆኑ ያሳያል። በተለምዶ፣ በማየትህ የምትደሰትበትን ሰው ስታይ፣ ሰላምታ ትሰጠዋለህ፤ እንዴት እንደሆነ እየጠየቅህም ማውራት ትጀምራለህ። በዚህ ስፍራ ግን ደቀ መዛሙርቱ እርሱን እያዳመጡ፣ ይህን ምግብ እየተቀበሉና ከሙታን ተነሥቶ በመካከላቸው የመገኘቱን ምሥጢር እያሰላሰሉ፣ በዚህ ቅዱስ አክብሮትና አድናቆት ውስጥ ቆዩ።
ጌታችን ወደ አንተ የሚመጣባቸውን መንገዶች ዛሬ አሰላስል። በሕይወታችን ውስጥ ያለው የማያቋርጥ መገኘቱም ምሥጢራዊ ስለሆነ፣ ሳናስተውለው ልንቀር እንችላለን። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ “መረቡን በጀልባው ቀኝ በኩል ጣሉ…” ብሎ ያቀረበላቸውን ጥሪ ችላ ቢሉት ኖሮ ምን ይሆን እንደነበር አስብ። ያንን ትእዛዝ ችላ ቢሉ ኖሮ፣ ጌታ መሆኑን ፈጽሞ ሳያውቁ ሊቀሩ ይችሉ ነበር። ጌታችን የሚያናግርህን መንገዶች አሰላስል። ምላሽ ትሰጣለህ? እርሱን ታውቀዋለህ? መለኮታዊ መገኘቱ ወደሚያሳድረው ወደዚህ ቅዱስ አክብሮትና አድናቆት እንድትሳብ ራስህን ትፈቅዳለህ? የደቀ መዛሙርቱን ምሳሌ ተከተል፤ በዙሪያህ ሁሉ ያለውን የጌታችንን የማያቋርጥ መገኘት ለማስተዋልም ንቁ ሁን።
አምላኬና ጌታዬ ሆይ፣ ቀንና ሌሊት ሳታቋርጥ ከእኔ ጋር ትገኛለህ፤ ሆኖም እጅግ ብዙ ጊዜ አንተን ማስተዋልና ማምለክ ይሳነኛል። በሕይወቴ ውስጥ መገኘትህን ይበልጥ እንዳስተውል እርዳኝ። ይህን ሳደርግም፣ በፍቅር፣ በትጋት፣ በአክብሮትና በአድናቆት ወደ እነዚህ ቅዱሳት ምሥጢራት ይበልጥ በጥልቀት እንድገባ እርዳኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
ስምንተኛ ቀን፦ ለእግዚአብሔር ምሕረት እሑድ መዘጋጃ የዘጠኝ ቀናት ጸሎት
ከላይ የቀረቡት ምስሎች፦ የጌታችንና የሐዋርያው ማዕድ፣ በጄምስ ቲሶ የተሣለ፣ በዊኪሚዲያ ኮመንስ በኩል





