ኦክቶበር 16, 2023
በመደበኛው ዘመን የሃያ ስምንተኛው ሳምንት ሰኞ
የዛሬ ንባባት
ቅድስት ማርጋሬት ማርያም አላኮክ፣ ድንግል—አማራጭ መታሰቢያ

“ይህ ትውልድ ክፉ ትውልድ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፣ ነገር ግን ከዮናስ ምልክት በቀር ሌላ ምልክት አይሰጠውም። ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደሆነ፣ የሰው ልጅም ለዚህ ትውልድ እንዲሁ ይሆናል።” ሉቃስ 11:29–30
ከእግዚአብሔር ምልክቶችን ስትፈልግ ራስህን ያገኘህበት ጊዜ አለ? ሁላችንም የምናልፍባቸውን የሕይወት ውጣ ውረዶች እያለፍን ስንጓዝ፣ በዚህ ወይም በዚያ ጉዳይ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚያሳዩ ምልክቶችን ከእግዚአብሔር ስንፈልግ ራሳችንን በቀላሉ ልናገኝ እንችላለን። እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ከሰማይ ምልክቶች በሆኑ ልዩ ጸጋዎች አማካይነት እንደሚናገረን የታወቀ ቢሆንም፣ ከላይ ያለው ክፍለ ንባብ ከሁሉ በላይ ትኩረት ልንሰጠው የሚገባን ምልክት የትኛው እንደሆነ ያብራራል።
በዚህ የወንጌል ክፍል ጌታችን የሚሰጠን ቀላል መልእክት፣ እስከ ዛሬ ከተሰጡት ሁሉ የጠለቀ ትርጉም ያለውን ምልክት ትርጉም ማወቅና ይህንንም በሕይወታችን ለምንወስናቸው ውሳኔዎች ሁሉ መሠረት ማድረግ እንዳለብን ነው። የኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የዘላለም ሕይወት ምንጭ ብቻ አልነበሩም፤ በሕይወታችን ውሳኔዎቻችንን ሁሉ ስንወስን የሚያስፈልገን ከሁሉ ግልጽ የሆነ ምልክትም ናቸው።
ምልክት ማለት ጥልቅና የተሰወረ ምሥጢርን የሚገልጥ ድርጊት ነው። የኢየሱስ ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ ከሚገልጡአቸው ምሥጢራት አንዱ ይህ ነው፤ በመስቀሉ ባስገኘልን አዲስ ሕይወት ለመካፈል ከፈለግን፣ ለራስ ጥቅም ሳይሆን ለሌሎች መሥዋዕት የሚሆን ሕይወት በመኖር የሰጠንን ምሳሌ መከተል አለብን። ሌሎች የክርስቶስን ትንሣኤ አዲስ ሕይወት እንዲያገኙና እንዲቀበሉ፣ ሕይወታችንን ስለ እነርሱ አሳልፈን መስጠት አለብን። በተግባር ስንመለከተው፣ በሕይወትህ መልሶችን ስትፈልግ፣ አንዳንድ ጊዜም ምን ማድረግ እንዳለብህ ምልክቶችን ከእግዚአብሔር ስትሻ ራስህን ካገኘህ፣ ዓይንህን ወደ ክርስቶስ ሕይወት መልስ። በዕለት ተዕለት ኑሮህ በምትወስነው እያንዳንዱ ተግባራዊ ውሳኔ ሕይወቱን ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ልትመስልባቸው የምትችልባቸውን መንገዶች አሰላስል። ይህም በሕይወትህ አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ወይም አንድ ትንሽ ተግባራዊ ውሳኔ ለመወሰን እያመዛዘንህ ብትሆንም እውነት ነው።
እንዲህ ያለውን ማመዛዘን ስናደርግ፣ ይበልጥ ለራሳችን ጥቅም በማድላት ራሳችንን መመልከታችን የተለመደ ነው። ከዚህ አስተሳሰብ መላቀቅ አስቸጋሪ ነው፤ ነገር ግን የሰው ልጅን “ምልክት” ለመጠቀም ከፈለግን፣ የሕይወታችንን ውሳኔዎች ፈጽሞ በተለየ መንገድ እናመዛዝናለን። የጌታችንን ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ በሕይወታችን ለምናደርገው ማመዛዘንና ለምንወስነው ውሳኔ ምንጭ ስናደርግ፣ በመጨረሻ የእርሱን ራስ ወዳድነት የሌለበት የፍቅር መሥዋዕት የሚመስሉ ውሳኔዎችን እንወስናለን። ስለዚህ፣ ውሳኔ የሚጠይቅ ጉዳይ ሲገጥምህ፣ የትኛው እንደሚቀልህ ወይም የትኛውን እንደምትመርጥ አታሰላስልም፤ ይልቁንም የትኛው ይበልጥ ከራስ ወዳድነት የራቀና ለሌሎች የተሻለ እንደሆነ ታሰላስላለህ። መሥዋዕት የሚሆነውን የኢየሱስን ፍቅር ከሁሉ በተሻለ የሚመስለው ምንድን ነው?
ዛሬ፣ ለመወሰን እየሞከርህ ያለኸውን ማንኛውንም ውሳኔ አሰላስል። ከዚያም ወደዚህ ውሳኔ እንዴት እየደረስህ እንደሆነ አሰላስል። ኢየሱስ የሰጠንን ምስክርነት ለማመዛዘንህ መሠረት ታደርጋለህን? ሕይወትህን ለሌሎች እንደ መሥዋዕት ስጦታ አሳልፈህ እንዴት ልትሰጥ እንደምትችል ታሰላስላለህን? ፍቅርን ከጌታችን መስቀል አንጻር ትመለከታለህን? የሚወዳቸውን ሰዎች ለማዳን ያሳየውን፣ ራስ ወዳድነት የሌለበትን ክቡር ራስን መስጠት ለመምሰል ትጥራለህን? የተግባሮቹን ምስክርነት በሕይወትህ ለምታደርገው ማመዛዘንና ለምትወስናቸው ውሳኔዎች ሁሉ መሠረት በማድረግ፣ ጌታችንን ለመምሰል ፈልግ። እንዲህም ስታደርግ፣ የሕይወትን ፈተናዎች ለማለፍ የሚያስፈልግህን ብቸኛውን እውነተኛ ምልክት አግኝተህ ትሆናለህ።
ፍጹም የሆንክ ጌታዬ ሆይ፣ በሕይወትህ የወሰንከው እያንዳንዱ ውሳኔ ከፍቅር የመነጨና ከአብ ፍጹም ፈቃድ ጋር የተስማማ ነበር። ፍጹም የሆነውን ምሳሌህን በመከተል በሕይወቴ እያንዳንዱን ውሳኔ ለመወሰን የሚያስፈልገኝን ጸጋ ስጠኝ። አንተ ሕይወትህን ለሌሎች አሳልፈህ እንደሰጠህ፣ ሕይወቴም አንተን ይምሰል። በሕይወቴ የምመራበት ምልክት እንድትሆን አንተንና መሥዋዕት የሆነውን ክቡር ሕይወትህን እመርጣለሁ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
አስፈላጊ፦ ለቅድስቲቱ ምድር ሰላም የጾም፣ ከሥጋ የመታቀብና የጸሎት ቀን
ለዓመቱ መደበኛ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ማሰላሰያዎች
የዕለቱ ቅዱሳን –
ከላይ የቀረበው ምስል፦ በዲሚትሪስ ቬትሲካስ፣ ከፒክሳቤይ




