አማርኛ

እውነተኛ ታላቅነት

ፌብሩዋሪ 27, 2024
የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ማክሰኞ
የዛሬ ንባቦች

የናሬክ ቅዱስ ጎርጎርዮስ፣ አበምኔትና የቤተ ክርስቲያን መምህር—የአማራጭ መታሰቢያ

ቪዲዮ

“ከእናንተ ሁሉ የሚበልጠው አገልጋያችሁ መሆን አለበት። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ግን ከፍ ይደረጋል።” ማቴዎስ 23:11–12

በእውነት ታላቅ መሆን ትፈልጋለህ? ሕይወትህ በሌሎች ሕይወት ውስጥ እውነተኛ ለውጥ እንዲያመጣ ትፈልጋለህ? ታላቅ የመሆን ይህን ምኞት ጌታችን በውስጣችን በጥልቅ አኑሮታል፤ ፈጽሞም አይጠፋም። በገሃነም ለዘላለም የሚኖሩት እንኳ ከተፈጥሯቸው ጋር ያለውን ይህን ምኞት ይዘው ይኖራሉ። ያ ምኞት ፈጽሞ ስለማይሟላላቸውም የዘላለም ሥቃያቸው ምክንያት ይሆናል። አንዳንድ ጊዜም ይህ የእኛ ዕጣ እንዳይሆን እንድንጠነቀቅ የሚያነሳሳን እንዲሆን፣ በዚህ እውነታ ላይ ማሰላሰል ጠቃሚ ነው።

በዛሬው ወንጌል ኢየሱስ ወደ ታላቅነት ከሚያደርሱን ቁልፎች አንዱን ይሰጠናል። “ከእናንተ ሁሉ የሚበልጠው አገልጋያችሁ መሆን አለበት።” አገልጋይ መሆን ማለት ከራስህ ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ መስጠት ማለት ነው። ለፍላጎቶችህ ትኩረት እንዲሰጡ ከመሞከር ይልቅ ለፍላጎቶቻቸው የላቀ ቦታ ትሰጣለህ። ይህን ማድረግም ከባድ ነው።

በሕይወት ውስጥ መጀመሪያ ስለ ራሳችን ማሰብ በጣም ቀላል ነው። ቁልፉ ግን በተግባር ከራሳችን ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ ስንሰጥ፣ በአንድ መልኩ ራሳችንን “በመጀመሪያ” እያስቀመጥን መሆናችን ነው። ምክንያቱም ለሌሎች ቅድሚያ ለመስጠት መምረጣችን ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን፣ ለእኛም ከሁሉ የሚሻለው ይኸው ስለሆነ ነው። የተፈጠርነው ለፍቅር ነው። የተፈጠርነው ሌሎችን ለማገልገል ነው። የተፈጠርነው የሚጠይቀንን መሥዋዕትነት ሳንቆጥር ራሳችንን ለሌሎች ለመስጠት ነው። ይህን ስናደርግ ግን ራሳችንን አናጣም። ከዚህ በተቃራኒው፣ ራሳችንን በመስጠትና ለሌላው ቅድሚያ በመስጠት ተግባር ውስጥ ነው በእውነት ማን እንደሆንን የምናውቀውና እንድንሆን የተፈጠርንለትን የምንሆነው። ፍቅር ራሱ እንሆናለን። የሚያፈቅር ሰውም ታላቅ ሰው ነው… ታላቅ ሰውም እግዚአብሔር ከፍ የሚያደርገው ሰው ነው።

ዛሬ ስለ ትሕትና ታላቅ ምሥጢርና ጥሪ አሰላስል። ለሌሎች ቅድሚያ መስጠትና እንደ አገልጋያቸው መሆን ቢከብድህም፣ አድርገው። በሁሉም ፊት ራስህን ዝቅ ለማድረግ ምረጥ። ለሚያሳስባቸው ጉዳዮች የላቀ ቦታ ስጥ። ለፍላጎቶቻቸው ትኩረት ስጥ። የሚሉትን አዳምጥ። ርኅራኄ አሳያቸው፤ ይህንንም እስከሚቻልህ ድረስ በተሟላ ሁኔታ ለማድረግ ዝግጁና ፈቃደኛ ሁን። እንዲህ ካደረግህ፣ በልብህ ጥልቅ ውስጥ የሚኖረው ታላቅ የመሆን ምኞት ይሟላል።

ትሑት ጌታዬ ሆይ፣ ስለ ትሕትናህ ምስክርነት አመሰግንሃለሁ። የኃጢአታችን ውጤት የነበሩትን ሥቃይና ሞት እስከ መቀበል ድረስ፣ ለሰዎች ሁሉ ቅድሚያ ለመስጠት መረጥህ። የተወደድክ ጌታ ሆይ፣ ፍጹም ፍቅርህን ለሌሎች ለማካፈል በእኔ እንድትሠራ፣ ትሑት ልብ ስጠኝ።  ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

የአሥራ ሁለተኛው ቀን ማሰላሰያዎች፦
40 ቀናት በበረሃ & 40 ቀናት በመስቀሉ ሥር

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

ለዐቢይ ጾም የሚረዱ ግብዓቶች

ለዐቢይ ጾም የመጽሐፍ ቅዱስ ማሰላሰያዎች

ሁሉም ቅዱሳን/በዓላት

የዕለቱ ቅዱስ – የናሬክ ቅዱስ ጎርጎርዮስ፣ አበምኔትና የቤተ ክርስቲያን መምህር

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ከላይ የቀረበው ዋና ምስል፦ ኢየሱስ የጴጥሮስን እግሮች ሲያጥብ፤ በፎርድ ማዶክስ ብራውን፣ በዊኪሚዲያ ኮመንስ በኩል