ፌብሩዋሪ 28፣ 2024
የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ረቡዕ
የዛሬ ንባባት

ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣ ሳለ፣ ዐሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ወደ ጎን ወስዶ በመንገድ ላይ እንዲህ አላቸው፦ «እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅም ለሊቃነ ካህናትና ለጸሐፍት አሳልፎ ይሰጣል፤ የሞት ፍርድም ይፈርዱበታል። ይዘባበቱበት፣ ይገርፉትና ይሰቅሉት ዘንድ ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ይነሣል።» ማቴዎስ 20:17–19
ያ ውይይት ምንኛ ከባድ ነበር! ከመጀመሪያው የሕማማት ሳምንት ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ኢየሱስ ከዐሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ፣ በኢየሩሳሌም ስለሚጠብቀው ነገር በግልጽና ያለ ስውር ተናገረ። ደቀ መዛሙርቱ ምን አስበው ሊሆን እንደሚችል አስቡ። በብዙ መልኩ፣ ይህ በዚያን ጊዜ ለእነርሱ ከመረዳት አቅማቸው በላይ ነበር። በብዙ መልኩም፣ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የሚናገረውን ነገር አለመስማትን መርጠው ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ግን፣ በተለይም የስቅለቱ ጊዜ እየቀረበ ሲመጣ፣ ይህን ከባድ እውነት መስማት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር።
ብዙ ጊዜ የወንጌልን ሙሉ መልእክት መቀበል ይከብደናል። ምክንያቱም የወንጌል ሙሉ መልእክት ሁልጊዜ በዋናነት ወደ መስቀሉ መሥዋዕት ይመራናል። ራስን መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅርንና መስቀልን ሙሉ በሙሉ መቀበልን ማየት፣ መረዳት፣ መውደድ፣ በሙላት መቀበልና በእርግጠኝነት ማወጅ ያስፈልጋል። ግን ይህ እንዴት ይሆናል? ከጌታችን ከራሱ እንጀምር።
ኢየሱስ እውነትን አልፈራም። ሥቃዩና ሞቱ መቃረባቸውን ያውቅ ነበር፤ ይህን እውነትም ያለ ማመንታት ለመቀበል ዝግጁ ነበር፣ ፈቃደኛም ነበር። መስቀሉን በአሉታዊ እይታ አላየውም። ሊወገድ የሚገባ አሳዛኝ ክስተት እንደሆነም አልቆጠረውም። ፍርሃት እንዲያስቆመው አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ፣ ኢየሱስ የተቃረበውን ሥቃዩን በእውነት ብርሃን ተመለከተው። ሥቃዩንና ሞቱን በቅርቡ የሚያቀርበው የከበረ የፍቅር ተግባር እንደሆነ አየው። ስለዚህም እነዚህን መከራዎች መቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ስለ እነርሱ በእርግጠኝነትና በድፍረት መናገርም አልፈራም።
በሕይወታችን አንድ ከባድ ነገር መጋፈጥ ባለብን ቁጥር፣ የኢየሱስን ድፍረትና ፍቅር እንድንመስል እንጋበዛለን። ይህ ሲሆን፣ በብዛት ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች አንዳንዶቹ፣ በችግሩ መቆጣት፣ ከእርሱ የምናመልጥበትን መንገድ መፈለግ፣ ሌሎችን መውቀስ ወይም ለተስፋ መቁረጥ እጅ መስጠትና መሰል ነገሮች ናቸው። በእንዲህ ያሉ ጊዜያት ችግርን ለመቋቋም የምንጠቀምባቸው ብዙ ልማዶች ወዲያውኑ ይነሣሉ፤ በእነዚህም አማካይነት የሚጠብቁንን መስቀሎች ለማስወገድ እንሞክራለን።
ይልቁንስ የጌታችንን ምሳሌ ብንከተልስ? የሚጠብቀንን እያንዳንዱን መስቀል በፍቅር፣ በድፍረትና በፈቃደኝነት ተቀብለን ብንጋፈጠውስ? መውጫ መንገድ ከመፈለግ ይልቅ፣ ለመናገር ያህል፣ መግቢያ መንገድ ብንፈልግስ? ይህም ማለት፣ ኢየሱስ መስቀሉን የተቀበለበትን ምሳሌ በመከተል፣ ሥቃያችንን ያለ ማመንታት፣ ራሳችንን መሥዋዕት በማድረግ የምንቀበልበትን መንገድ ብንፈልግስ? በሕይወት የሚያጋጥመን እያንዳንዱ መስቀል በራሳችንም ሆነ በሌሎች ሕይወት የብዙ ጸጋ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ፣ ከጸጋና ከዘላለም አንጻር ስንመለከት፣ መስቀሎችን መቀበል እንጂ መሸሽ ወይም መርገም የለብንም።
ዛሬ እየተጋፈጣችሁት ስላለው ማንኛውም ችግር አሰላስሉ። ኢየሱስ በሚያይበት መንገድ ታዩታላችሁ? የተሰጣችሁን እያንዳንዱን መስቀል ራስን መሥዋዕት ለሚያደርግ ፍቅር እንደ አጋጣሚ ማየት ትችላላችሁ? እግዚአብሔር ከእርሱ መልካም ነገር ሊያወጣ እንደሚችል እያወቃችሁ፣ በተስፋና በእርግጠኝነት መቀበል ትችላላችሁ? የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች በደስታ በመቀበል ጌታችንን ለመምሰል ጣሩ፤ እነዚያም መስቀሎች በመጨረሻ ከጌታችን ጋር በትንሣኤ ይካፈላሉ።
መከራን የተቀበልክ ጌታዬ ሆይ፣ በመስቀል ላይ የደረሰብህን ግፍ በፍቅርና በድፍረት፣ በገዛ ፈቃድህ ተቀበልክ። በግልጽ ከሚታየው ማሰናከያና ሥቃይ ባሻገር ተመለከትክ፤ በአንተ ላይ የተፈጸመውንም ክፋት እስከ ዛሬ ከታወቁት ሁሉ ወደሚበልጥ የፍቅር ተግባር ለወጥከው። ፍጹም ፍቅርህን እንድመስል፣ ይህንንም አንተ በነበረህ ብርታትና እርግጠኝነት እንዳደርግ ጸጋህን ስጠኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
የአሥራ ሦስተኛው ቀን ማሰላሰያዎች፦
40 ቀናት በበረሃ & 40 ቀናት በመስቀሉ ሥር
ከላይ የቀረበው ምስል፦ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲነጋገር፤ በ ጄምስ ቲሶ፣ በዊኪሚዲያ ኮመንስ በኩል




