አማርኛ

የተጨነቀ ልብ

ሜይ 17, 2022
የፋሲካ አምስተኛ ሳምንት ማክሰኞ
የዛሬ ንባባት

ቪዲዮ

“ልባችሁ አይጨነቅ፣ አይፍራም።” ዮሐንስ 14:27

ሁላችንም በየጊዜው መስማት የሚያስፈልገን እንዴት ያለ ድንቅ ማሳሰቢያ ነው! “ልብህ አይጨነቅ።” ደግሞም፣ “ልብህ አይፍራ።” ይህን ምክር ምን ያህል ጊዜ ትከተላለህ?

የሚያስደንቀው፣ ይህ ከምክርም በላይ መሆኑ ነው። ከጌታችን የተሰጠ የፍቅር ትእዛዝ ነው። ጌታችን ይህን ግልጽ ማድረግ ይፈልጋል፤ በፍርሃትና በጭንቀት የተሞላ ልብ ከእርሱ እንዳልሆነም እንድናውቅ ይፈልጋል። መጨነቅና መፍራት የሚያደክመን ከባድ ሸክም ነው። ኢየሱስ ከእነዚህ ሸክሞች ነፃ እንድንሆን እጅግ አጥብቆ ይፈልጋል። የሕይወትን ደስታ እንድናጣጥም ነፃ እንድንሆን ይፈልጋል።

ታዲያ በሕይወትህ ከሁሉ በላይ የሚከብድብህ ሸክም ምንድን ነው? በሕይወትህ ያለማቋረጥ የምታስብበት፣ የምትቆጣበት፣ መተው ያልቻልከው ወይም ሕይወትህን የሚቆጣጠር ነገር አለ? ወይስ ሸክምህ በቀላሉ የማይታወቅ ይሆን? ምናልባት ሙሉ በሙሉ የሚያዳክምህ ነገር ላይኖር ይችላል፤ ይልቁንም በትንሹ የሚጫንህ፣ ሁልጊዜም ከኋላ ሆኖ አብሮህ የሚቆይ ሸክም ሊኖር ይችላል። እነዚህ ሸክሞች ከዓመት ዓመት ሲቀጥሉ እጅግ አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ።

ወደ ነፃነት የሚወስደው የመጀመሪያው እርምጃ ሸክሙን በእውነተኛ መልኩ ማየት ነው። ሸክሙ ምን እንደሆነ ለይ፤ ከሥሩ ያለውን ምክንያትም ለማወቅ ሞክር። የሸክምህ መንሥኤ የራስህ ኃጢአት ከሆነ፣ ከዚያ ኃጢአት ተመለስ፣ ወደ ምሥጢረ ንስሐም ቅረብ። ወዲያውኑ ነፃነትን ለማግኘት ይህ ሁሉን የሚበልጥ መንገድ ነው።

ነገር ግን ሸክምህ በሌላ ሰው ድርጊት ወይም ከአቅምህ በላይ በሆነ የሕይወት ሁኔታ የተከሰተ ከሆነ፣ ይህን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ በጌታችን እጅ አስገብተህ ራስህን ለእርሱ ለማስረከብ ልዩ አጋጣሚ አለህ። ነፃነት የሚገኘው ራስን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ በማስረከብ፣ በእርሱ በመታመንና ሁሉን ለፈቃዱ በመተው ነው።

ዛሬ በሕይወትህ ከሁሉ በላይ ስለሚከብድብህ ሸክም ለማሰላሰል ጥቂት ጊዜ ውሰድ። እጅግ የሚጫንህ ምንድን ነው? ኢየሱስ ከሌላው ሁሉ በላይ ገብቶ ሊያነሣልህ የሚፈልገው ይህንኑ ሸክም ነው። በሕይወትህ ሊሰጥህ የሚፈልገውን ደስታ እንድታጣጥም ነፃ እንድትሆን ይፈልጋል።

የእውነተኛ ደስታ ጌታ ሆይ፣ ነፃ መሆን እፈልጋለሁ። ለእኔ ያዘጋጀኸውን ደስታ ማጣጣም እፈልጋለሁ። የሕይወት ሸክሞች ሲጫኑኝ፣ በችግሬ ወደ አንተ እንድዞር እርዳኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

የፋሲካ ጸሎቶች

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ከላይ የቀረበው ምስል፦ ክርስቶስና ሀብታሙ ወጣት አለቃ፣ በሃይንሪክ ሆፍማን የተሣለ፣ ከዊኪፔዲያ የተገኘ


  Subscribe to our YouTube channel  
  to be notified about new content.