አማርኛ

ወሰንና ቅድመ ሁኔታ የሌለው ፍቅር

ግንቦት 19, 2022
በትንሣኤ ዘመን የአምስተኛው ሳምንት ሐሙስ
የዛሬ ንባቦች

ቪዲዮ

“አብ እንደሚወደኝ፣ እኔም እንዲሁ እወዳችኋለሁ።”  ዮሐንስ 15:9

ከዚህ ክፍለ ንባብ ልንቀስማቸው የሚገቡ ሦስት ውብ ግንዛቤዎች አሉ።  

አንደኛ፣ አብ ለወልድ ያለው ፍቅር በሁሉም ረገድ ፍጹም ነው።  ቅድመ ሁኔታ የሌለውና መላ ማንነትን የሚያጥለቀልቅ ነው።  ሙሉና ከራስ ወዳድነት የራቀ ነው።  ኢየሱስ የአብን ፍቅር ሲቀበል፣ የሚያስፈልገውን ሁሉ ይቀበላል።  

ሁለተኛ፣ ኢየሱስ ከአብ የሚቀበለው ፍቅር ተወስኖ ሊቀር አይችልም።  ለራሱ ብቻ ሊያስቀረው አይችልም።  የአብ ፍቅር ከኢየሱስ ልብ ተትረፍርፎ የሚፈስ ፍቅር ነው።  ከኢየሱስ ወደ እኛ የሚፈሰውም ይህ የሚትረፈረፍ ፍቅር ነው።  

ሦስተኛ፣ በዚህ ውስጥ ልናሰላስለው የሚገባ ቁልፍ ነገር፣ አሁን ለእኛ የተሰጠው ይህ የሚትረፈረፍ ፍቅር በእኛም ውስጥ ብቻ ተወስኖ ሊቀር እንደማይችል ነው።  ከልባችን ተትረፍርፎ ወደ ሌሎች መፍሰስ አለበት።  ስለዚህ፣ የአብና የወልድን ፍቅር በእውነት የምንቀበል ከሆነ፣ እኛም በተራችን ያ ፍቅር “ያለ ወሰን” እና “ያለ ቅድመ ሁኔታ” ወደ ሌሎች እንዲፈስ መፍቀድ አለብን።

እስቲ አስብበት።  “ያለ ወሰን።”  “ያለ ቅድመ ሁኔታ።”  ይህ በእውነት ይቻላልን?  ሌሎችን በመውደዳችን እስከዚህ ድረስ መሠረታዊና ሙሉ ለውጥ ማሳየት ይቻላልን?  አዎን፣ ሊቻል የሚችለው ግን የምንናገርለት ፍቅር ከአብ ልብ የሚመነጭ፣ ለወልድ የተሰጠ፣ ከዚያም በነፃ እንድናካፍለው በእኛ ላይ የፈሰሰ ከሆነ ብቻ ነው።  

ለሌሎች እንድታካፍለው የተጠራኸው ፍቅር ምንጩ የሰማያዊው አባት ልብ መሆኑን ዛሬ አሰላስል።  በአባት ልብ መውደድን ለመማር የመጀመሪያውና ከሁሉ አስፈላጊው እርምጃ፣ እግዚአብሔር እንዲወድህ መፍቀድ ነው።  ይህን ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።  እግዚአብሔር እንዲወድህ መፍቀድ፣ ያን ፍቅር መቀበልና በጥልቅ እንዲነካህ መፍቀድ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።  ነገር ግን እግዚአብሔር በፍጹም ፍቅሩ እንዲወድህ ያለማቋረጥ መፍቀድ ከቻልክ፣ ይህ ፍቅር እንደሚትረፈረፍ የጸጋና የምሕረት ወንዝ ከአንተ በራሱ መፍሰሱን ማየት ትጀምራለህ።

አፍቃሪ አባትና ወልድ ሆይ፣ በእውነት እወዳችኋለሁ፤ እናንተም እንደምትወዱኝ አውቃለሁ።  ለፍቅራችሁ ልቤን እንድከፍት እርዱኝ። ያ ፍቅር ከልቤ ተትረፍርፎ ወደ ሌሎችም እንዲፈስ፣ በውስጤ በጥልቅ እንዲሰርጽ እርዱኝ።  ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

የፋሲካ ጸሎቶች

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ከላይ የቀረበው ምስል፦ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ፣ በፖምፔዮ ባቶኒ የተሳለ፣ በዊኪሚዲያ ኮመንስ በኩል


  Subscribe to our YouTube channel  
  to be notified about new content.