አማርኛ

ሐቀኛ መሆን

ጁን 13, 2020
በዓመቱ የተለመደው ዘመን አሥረኛ ሳምንት ቅዳሜ
የዛሬ ንባቦች

የፓዱዋው ቅዱስ አንጦንዮስ፣ ካህንና የቤተ ክርስቲያን መምህር—መታሰቢያ

“‘አዎ’ የምትሉት ‘አዎ’፣ ‘አይ’ የምትሉትም ‘አይ’ ይሁን። ከዚህ የሚበልጠው ሁሉ ከክፉው ነው።” ማቴዎስ 5:37

ይህ ትኩረትን የሚስብ ቃል ነው። መጀመሪያ ላይ፣ “ከዚህ ሌላ ያለው ሁሉ ከክፉው ነው” ማለት ትንሽ የተጋነነ ይመስላል። ነገር ግን እነዚህ የኢየሱስ ቃላት ስለሆኑ፣ ፍጹም እውነት የሆኑ ቃላት ናቸው። ታዲያ ኢየሱስ ምን ማለቱ ነው?

ኢየሱስ ይህን ቃል የተናገረው መሐላ ማድረግን በተመለከተ ስለ ትክክለኛ ሥነ ምግባር ሲያስተምረን ነው። ትምህርቱ በመሠረቱ በስምንተኛው ትእዛዝ ውስጥ የሚገኘውን “እውነተኛ መሆን” የሚለውን መሠረታዊ መርሕ ያቀርባል። ኢየሱስ ሐቀኞች እንድንሆን፣ የምናስበውን እንድንናገርና የምንናገረውም ከልባችን እንዲሆን እየነገረን ነው።

ኢየሱስ ስለ መሐላ በሚሰጠው ትምህርት ውስጥ ይህን ከሚያነሣባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ በተለመዱ ዕለታዊ ውይይቶቻችን ውስጥ በክብርና በቁም ነገር የሚፈጸም መሐላ ሊያስፈልግ አይገባም የሚለው ነው። እርግጥ ነው፣ እንደ ጋብቻ ስእለቶች ወይም ካህናትና የተቀደሰ ሕይወት አባላት በክብርና በቁም ነገር እንደሚገቧቸው ስእለቶችና ቃል ኪዳኖች ያሉ ልዩ ክብር ያላቸው መሐላዎች አሉ። እንዲያውም በእያንዳንዱ ምሥጢር ውስጥ በሆነ መልክ በክብርና በቁም ነገር የሚገባ ቃል አለ። ሆኖም የእነዚህ ቃል ኪዳኖች ባሕርይ፣ ሰዎችን በቃላቸው ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ እምነትን በአደባባይ መግለጽ ነው።

እውነቱ ግን፣ ሐቀኞችና ቅን ሰዎች እንድንሆን የሚጠራን ስምንተኛው ትእዛዝ በዕለታዊ ተግባራችን ሁሉ በቂ ሊሆን ይገባል። ስለዚህ ወይም ስለዚያ ጉዳይ “በእግዚአብሔር እምላለሁ” ማለት አያስፈልገንም። በዚህም ሆነ በዚያ ሁኔታ እውነት እየተናገርን መሆናችንን ሌላውን ለማሳመን የግድ እንደሚያስፈልገን ሊሰማን አይገባም። ከዚህ ይልቅ፣ ሐቀኞችና ቅን ሰዎች ከሆንን፣ ቃላችን በቂ ይሆናል፤ የምንለውም እኛ ስለተናገርነው ብቻ እውነት ይሆናል።

ዛሬ፣ በሕይወትህ ዘርፎች ሁሉ ምን ያህል ሐቀኛ እንደሆንህ አሰላስል። በሕይወትህ ትልቅም ሆነ ትንሽ ጉዳዮች እውነትን የመናገር ልማድ አዳብረሃልን? ሰዎች ይህን ባሕርይ በአንተ ውስጥ ያያሉን? እውነትን መናገርና የእውነት ሰው መሆን፣ በተግባራችን ወንጌልን የምናበስርባቸው መንገዶች ናቸው። ዛሬ ሐቀኛ ለመሆን ቁርጥ ውሳኔ አድርግ፤ ጌታም በምትናገረው ቃል አማካይነት ታላቅ ነገር ያደርጋል።

ጌታ ሆይ፣ ሐቀኛና ቅን ሰው እንድሆን እርዳኝ። እውነትን ባጣመምሁባቸው፣ በረቀቁ መንገዶች ባታለልሁባቸውና በግልጽ በዋሸሁባቸው ጊዜያት እጸጸታለሁ። “አዎ” የምለው ሁልጊዜ ከፍጹም ቅዱስ ፈቃድህ ጋር እንዲስማማ እርዳኝ፤ ከስሕተት መንገዶችም ሁልጊዜ እንድመለስ እርዳኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ የሚቀርብ የዘጠኝ ቀን ጸሎት
የዘጠኝ ቀን ጸሎቱ ቀናት፦ጁን 10-18, 2020
ጁን 19, 2020፦ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ታላቅ በዓል

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

ሁሉም ቅዱሳን/በዓላት

የዕለቱ ቅዱስ – የፓዱዋው ቅዱስ አንጦንዮስ፣ ካህንና የቤተ ክርስቲያን መምህር

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች