ሴፕቴምበር 7, 2020
በዓመቱ መደበኛ ዘመን የሃያ ሦስተኛው ሳምንት ሰኞ
የዛሬ ንባባት

«እጅህን ዘርጋ።» እርሱም እንዲሁ አደረገ፣ እጁም ዳነች። እነርሱ ግን በቁጣ ተሞልተው በኢየሱስ ላይ ምን ሊያደርጉ እንደሚችሉ እርስ በርሳቸው ተመካከሩ። ሉቃስ 6:10-11
ይህ እጅግ የሚረብሽ ክፍል ነው። ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ሆን ብለውና አስበውበት በታላቅ ተንኮል ይሠሩ እንደነበር በተደጋጋሚ እናያለን። በዚህም ኢየሱስን ሊከሱበት የሚችሉትን ማንኛውንም ድርጊት ይፈልጉ ነበር። ታዲያ ሊከሱት የሚችሉበት ምን ነገር አገኙ? በሰንበት ቀን ተአምር ሲያደርግ አዩት። ይህም ኢየሱስ የሠራው ኃጢአት ይመስል ነበር የተገበሩት። በእውነት?
ይህ ክፍል እጅግ የሚረብሸው፣ በዚያን ጊዜ የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ እንደነበር ግልጽ ስለሆነና ኢየሱስም ለራሳቸው የሚሰጡትን ታላቅ ግምት እየተጋፋ ስለነበር ነው። እርሱ ከጸሐፍትና ከፈሪሳውያን ይልቅ በሕዝቡ ዘንድ እየተወደደና እየተከበረ ነበር፤ እነርሱም በምቀኝነት ተሞሉ።
ከዚህ ክፍል የምንማረው አንድ አስፈላጊ ነጥብ፣ የምቀኝነት ኃጢአት ከምክንያት ውጭ እንድናስብና በሞኝነት እንድንመላለስ የሚያደርገን መሆኑ ነው። ይህ ኃጢአት ያሳውረናል፤ የሞኝነት ነገሮችንም እንድናስብና እንድንናገር ያደርገናል። ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ያደረጉት ይህንኑ ነው። ጤናማ አእምሮ ያለው ማን ነው ኢየሱስ በሰንበት እንደ መፈወስ ያለ መልካም ነገር በማድረጉ «የሚከሰው»? በምቀኝነት የታወሩ ብቻ ናቸው።
ይህ ክፍል የሚረብሽ ቢሆንም፣ ይህ መረበሽ ጠቃሚ እንዲሆንልን ተስፋ ይደረጋል። ለእያንዳንዳችን የራሳችንን ሕይወት ለመመልከትና ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለመመርመር አጋጣሚ ሊሆንልን ይገባል። ከእነዚህ ግንኙነቶች በአንዱ ውስጥ ምቀኝነት እንዳለ ታያለህ? አንዳንድ ጊዜ በዚህ ወይም በዚያ ሰው ላይ ያለ ምክንያት እያሰብክና እየተገበርክ ራስህን ታገኛለህ?
ዛሬ፣ እንደ ጸሐፍትና ፈሪሳውያን ለመሆን በውስጥህ ሊኖር በሚችል ማንኛውም ዝንባሌ ላይ አሰላስል። ድርጊታቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የተካተተው፣ አንዳንድ ጊዜ ስለምንታገለው ስለዚህ አስቀያሚ ኃጢአት እኛን ለማስተማር መሆኑን እወቅ። የዚህ ክፍል የሚረብሽ ገጽታ በሕይወትህ ከምቀኝነት ነፃ ለመውጣት እንድትጥር ያነሳሳህ።
ጌታ ሆይ፣ ከትዕቢት፣ ከምቀኝነትና ከቅናት ኃጢአቶች ነፃ መሆንን በእውነት እፈልጋለሁ። በሕይወቴ ውስጥ እነዚህን እንዳይ፣ ከእነርሱም በንስሐ እንድመለስና በእነርሱ ፋንታ ምሕረትህንና ፍቅርህን እንዳኖር እርዳኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
ምስል፦ ክርስቶስ እጁ ሽባ የሆነውን ሰው ይፈውሳል። በሞንሬያሌ ካቴድራል የሚገኝ የባይዛንታይን ሞዛይክ ሥዕል።




