አማርኛ

እውነታን በመካድ ውስጥ መጣበቅ

ኤፕሪል 13, 2022
የሳምንተ ሕማማት ረቡዕ
የዛሬ ንባቦች

ቪዲዮ

የሰው ልጅ ስለ እርሱ እንደ ተጻፈው በእርግጥ ይሄዳል፤ ነገር ግን የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ሰው ወዮለት። ያ ሰው ባልተወለደ ይሻለው ነበር።” ከዚያም አሳልፎ የሚሰጠው ይሁዳ፣ “ረቢ ሆይ፣ እኔ አይደለሁም እኮ?” ብሎ መለሰ። እርሱም፣ “አንተ አልክ” አለው።  ማቴዎስ 26:24–25

ይሁዳ እውነታውን እየካደ ነበርን?  ኢየሱስን አሳልፎ የሚሰጠው እርሱ እንዳልሆነ በእውነት አስቦ ነበርን?  በይሁዳ አእምሮ ውስጥ ምን ይመላለስ እንደነበር በእርግጠኝነት አናውቅም፤ አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው… ኢየሱስን አሳልፎ ሰጥቷል።  ከቃላቱም እንደሚታየው፣ ድርጊቱን አሳልፎ እንደ መስጠት አልቆጠረውም፤ ስለዚህም እውነታውን በጥልቅ እየካደ ነበር።

መካድን የሚያመለክተው የእንግሊዝኛ ቃል እንደ ምሕፃረ ቃል ሲፈታ፣ “እየዋሸሁ መሆኔን እንኳ አላውቅም” ማለት ነው ተብሏል።  ምናልባት ይሁዳ በራሱ ኃጢአት ውስጥ እጅግ ከመዘፈቁ የተነሣ፣ እየዋሸ እንደነበርና ኢየሱስን በገንዘብ አሳልፎ ለመስጠት እየተዘጋጀ እንደነበር፣ ለሌሎች ይቅርና ለራሱ እንኳ ማመን አልቻለም ይሆናል።  ይህ አስፈሪ ሐሳብ ነው።

አስፈሪ የሆነውም በኃጢአት መጽናት ከሚያስከትላቸው ውጤቶች አንዱን ስለሚገልጥ ነው።  በኃጢአት መጽናት፣ ኃጢአትን መፈጸም ቀላል እንዲሆን ያደርጋል።  በመጨረሻም አንድ ሰው በዚያው ኃጢአት ሲጸና፣ ለዚያ ኃጢአት ምክንያት መደርደር፣ ትክክል እንደሆነ ማስመሰልና ጭራሹኑ ኃጢአት መሆኑን መካድ ቀላል ይሆናል።  አንድ ሰው በኃጢአት እየጸና ወደ ታች በሚያወርደው በዚህ አዙሪት ውስጥ ሲጣበቅ፣ ከእርሱ መውጣት ከባድ ነው።  ብዙ ጊዜም ከሥነ ልቦናዊው ውጥረት ለመትረፍ የሚቀረው ብቸኛ መንገድ፣ እውነታውን መካዱን መቀጠል ይሆናል።

በዚህ የሕማማት ሳምንት ይህ ለእኛ ጠቃሚ ትምህርት ነው።  ኃጢአትን መመልከት ፈጽሞ ደስ አይልም፤ ይህን ለማድረግም ታላቅ ድፍረት ይጠይቃል።  ነገር ግን ይሁዳ ሊያደርገው የነበረውን ነገር በእርግጥ ተናዝዞ ቢሆን ኖሮ ምን ይሆን እንደነበር አስብ።  በኢየሱስና በሌሎቹ ሐዋርያት ፊት በሐዘን ተሰብሮ እውነቱን ሁሉ ቢነግራቸው ኖሮ ምን ይሆን እንደነበር አስብ።  ምናልባት ያ ሐቀኛ ድርጊት ሕይወቱንና ለዘላለም የምትኖረውን ነፍሱን ያድን ነበር።  እንዲህ ማድረግ ለእርሱ አሳማሚና አዋራጅ ይሆን ነበር፤ ሆኖም ትክክለኛው ማድረግ ያለበት ነገር ይህ ነበር።

ስለ አንተም እውነቱ ይህ ነው።  ምናልባት ኃጢአትህ ኢየሱስን በግልጽ አሳልፎ ወደ መስጠት እየመራህ ባለበት ደረጃ ላይ ላትሆን ትችላለህ፤ ሆኖም በዚህ የሕማማት ሳምንት እያንዳንዱ ሰው በሕይወቱ ውስጥ የሆነ ተደጋጋሚ የኃጢአት ባሕርይ ሊያገኝ ይችላል።  በእግዚአብሔር እርዳታ፣ ያዳበርከውን የሆነ ተደጋጋሚ ባሕርይ ወይም ልማድ ለማወቅ መጣር አለብህ።  ከዚያም ይህን ኃጢአት በቅንነትና በድፍረት ልትጋፈጠው ብትችል፣ ይህ እንዴት ያለ ታላቅ ግኝት ይሆንልህ ነበር!  ይህም ኃጢአትህን በተመለከተ ያለብህን ማንኛውንም የመካድ ዝንባሌ ለማስወገድና ያንን ኃጢአት ድል ለማድረግ ያስችልሃል፤ በዚህም እግዚአብሔር እንድትለማመደው የሚፈልገውን ነፃነት ታገኛለህ!

ዛሬ ይሁዳ ኢየሱስን፣ “ረቢ ሆይ፣ እኔ አይደለሁም እኮ?” ማለቱን አሰላስል።  ጌታችን ይሁዳ እውነታውን ሲክድ ሲያይ፣ ይህ የይሁዳ አሳዛኝ ንግግር ልቡን በጥልቅ አቁስሎት መሆን አለበት።  አንተም ከልብ ንስሐ መግባት ተስኖህ ኃጢአትህን የምትክድባቸውን ብዙ ጊዜያት አሰላስል።  ይህን የሕማማት ሳምንት የቅንነትና የሐቀኝነት ጊዜ አድርገው።  የጌታ ምሕረት እጅግ ጥልቅና ንጹሕ ስለሆነ፣ ብትረዳው ኖሮ፣ ኃጢአቶችህን በማንኛውም መልኩ እየካድክ መቆየት ባላስፈለገህ ነበር።

ርኅሩኅ ጌታዬ ሆይ፣ በዚህ ሳምንተ ሕማማት ኃጢአቴንና ድካሜን ለመጋፈጥ የሚያስፈልገኝን ድፍረት እንዳገኝ እርዳኝ። ውድ ጌታዬ ሆይ፣ እኔ ኃጢአተኛ ነኝ፤ ይህን ማመን ግን እጅግ ሊከብደኝ ይችላል። ነፃ እንድወጣና በኃጢአቴ ፈንታ የተትረፈረፈ ምሕረትህን እንድቀበል፣ ኃጢአቴን በእጅህ አደራ ልስጥ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ከብፅዕት እናታችን ልብ የሚመነጭ የፍቅር እይታ
አስተንትኖ አርባ – የመቃብሩ ዝምታ
(የሳምንተ ሕማማት ረቡዕ)

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

ለዐቢይ ጾም የሚረዱ ግብዓቶች

ለዐቢይ ጾም የመጽሐፍ ቅዱስ ማሰላሰያዎች

የሕማማት ሳምንት ጸሎቶች

ሁሉም ቅዱሳን/በዓላት

የዕለቱ ቅዱስ – ቅዱስ ማርቲን ቀዳማዊ፣ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳትና ሰማዕት
(የመታሰቢያው ቀን በሳምንተ ሕማማት ስለሚውል፣ በዚህ ዓመት በሥርዓተ አምልኮ አይከበርም)

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ከላይ የቀረበው ምስል፦ የመጨረሻው እራት፤ በካርል ብሎክ፣ በዊኪሚዲያ ኮመንስ በኩል