አማርኛ

የቁጣ ሸክም

ጁን 15፣ 2023
በመደበኛው ዘመን የአሥረኛው ሳምንት ሐሙስ
የዛሬ ንባቦች

ቪዲዮ

“ለአባቶቻችሁ፣ አትግደል፤ የሚገድልም ሁሉ ለፍርድ ይቀርባል እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፤ በወንድሙ የሚቆጣ ሁሉ ለፍርድ ይቀርባል፤ ወንድሙን ራቃ የሚልም ሁሉ በሳንሄድሪን ፊት ተጠያቂ ይሆናል፤ ‘አንተ ሰነፍ’ የሚልም ሁሉ ለገሃነመ እሳት ይዳረጋል።” ማቴዎስ 5:21–22

ከላይ የተጠቀሰው ክፍል በሌላ ሰው ላይ የምንፈጽማቸውን፣ እየከበዱ የሚሄዱ ሦስት የኃጢአት ደረጃዎች ያሳየናል። እነዚህን ኃጢአቶች የሚመለከቱት ትምህርቶች በብሉይ ኪዳን ያልተካተቱ አዳዲስ ትምህርቶች ነበሩ። በዚህ ትምህርት፣ ኢየሱስ ወደ ጥልቅ ቅድስናና የባልንጀራ ፍቅር የሚያቀርበው ጥሪ እጅግ ግልጽ ይሆናል።

የመጀመሪያው የኃጢአት ደረጃ በውስጥ ብቻ “መቆጣት” ነው። የቁጣ ኃጢአት በሌላ ሰው ላይ በውስጥ የሚኖር የጥላቻ አመለካከት ነው። ኢየሱስ በሌላ ሰው ላይ ቁጣ መያዝ “ለፍርድ መቅረብን” እንደሚያስከትል ይናገራል። ሁለተኛው የኃጢአት ደረጃ ሌላውን ሰው “ራቃ።” ስትል ነው። ይህን የአራማይክ ቃል መተርጎም አስቸጋሪ ቢሆንም፣ አንድ ሰው በሌላው ላይ ያለውን ቁጣ የሚገልጽበትን አንድ ዓይነት አነጋገር ያካትታል። ሌላውን ሰው አእምሮ የሌለው ወይም ዝቅተኛ እንደሆነ በማዋረድ የሚነገር አባባል ነው። ኢየሱስ የጠቀሰው ሦስተኛው የኃጢአት ደረጃ ሌላውን ሰው “ሰነፍ” ብለህ ስትጠራው ነው። ይህ ቃል ከራቃ ይልቅ የጠነከረ አገላለጽ ነው፤ ሰውየው በሥነ ምግባር ረገድ የጠፋ ነፍስ እንደሆነ የሚያመለክት የቃል ወቀሳም ነው። ይህም በሌላው ሰው ሥነ ምግባር ላይ የሚገለጽ ከባድ ውግዘት ነው።

ታዲያ፣ ከቁጣ ጋር ትታገላለህ? ኢየሱስ ከዚህ ኃጢአት ከሁሉም ደረጃዎች ነፃ እንድንሆን የሚያቀርበው ጥሪ ከፍ ያለ ነው። በሕይወታችን ውስጥ የቁጣ ስሜታችን በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የሚቀሰቀስባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ፤ ያም ስሜት ከእነዚህ የኃጢአት ደረጃዎች ወደ አንዱ ይመራናል። የተቆጣኸውን ሰው በሚቻለው ሁሉ በጣም አጥብቀህ ለማውገዝ መፈለግ የተለመደ ፈተና ነው።

ይህ አዲስ የኢየሱስ ትምህርት ተረድተን ስንቀበለው፣ በእርግጥ ሸክም እንዳልሆነ ማወቅ አስፈላጊ ነው። መጀመሪያ ላይ እነዚህ ቁጣን የሚቃወሙ የጌታችን ሕጎች አሉታዊ ሊመስሉ ይችላሉ። ይህም የሚሆነው ሌላውን ሰው በቁጣ መውረፍ የሐሰት እርካታ ስለሚሰጥ ነው፤ እነዚህ የጌታችን ትእዛዛትም በአንድ መልኩ ያንን እርካታ “ይነጥቁብናል።” ሥርዓት ያጣ ቁጣ እስኪወገድ ድረስ ይቅር የማለት ሥነ ምግባራዊ ግዴታ እንዳለብን ማሰብ የሚያስጨንቅ ሊመስል ይችላል። ግን በእርግጥ የሚያስጨንቅ ነውን? ይህ የጌታችን ሕግ ሸክም ነውን?

ጥልቁ እውነት ግን፣ ኢየሱስ በዚህ ክፍል የሚያስተምረን በብዙ መልኩ ከሌሎች ጥቅም ይልቅ ለራሳችን ጥቅም መሆኑ ነው። በሌላ ሰው ላይ ያለን ቁጣ፣ በውስጣችን ብቻ የሚቀርም ሆነ በቃል በመውቀስ ወይም ፈጽሞ በማውገዝ የሚገለጽ፣ የተቆጣነውን ሰው ሊጎዳ ይችላል፤ ሆኖም እነዚህ የቁጣ ዓይነቶች በእኛ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት በእርሱ ላይ ከሚያደርሱት እጅግ የከፋ ነው። በውስጣችን ብቻ ብንቆጣም፣ ደስተኛ መስለን ብንታይም እንኳ፣ መቆጣት ነፍሳችንንና ከእግዚአብሔር ጋር አንድ የመሆን ችሎታችንን እጅግ ይጎዳል። ስለዚህ ሸክም የሆነው ይህ ቁጣን የሚመለከት አዲስ የጌታችን ሕግ አይደለም፤ ይልቁንም ከባድ ሸክም የሆነው ቁጣው ራሱ ነው፤ ኢየሱስም ከዚህ ሸክም ነፃ እንድትሆን ይፈልጋል።

ዛሬ ስለ ቁጣ ኃጢአት አሰላስል። ይህን ስታደርግ፣ እውነተኛው ጠላትህ የተቆጣኸው ሰው ሳይሆን ሥርዓት ያጣው ቁጣህ እንደሆነ ለማየት ሞክር። ጌታችን ከዚህ የነፍስ ጠላት ነፃ እንዲያወጣህ ጸልይ፤ ሊሰጥህ የሚፈልገውንም ነፃነት ፈልግ።

መሐሪ ጌታዬ ሆይ፣ ሸክም ከሚሆንብን ሁሉ ፈጽሞ ነፃ እንድንሆን ትጠራናለህ። ቁጣ ሸክም ይሆንብናል። ቁጣዬ በእኔ ላይ የሚጭነውን ሸክም እንዳይ እርዳኝ፤ ይቅር በማለትና በመታረቅም እውነተኛ ነፃነትን እንድፈልግ እርዳኝ። የተወደድክ ጌታ ሆይ፣ እኔን የጎዱኝን ሁሉ ይቅር እንደምል፣ እባክህ ይቅር በለኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ የሚቀርብ የዘጠኝ ቀን ጸሎት
የዘጠኙ ቀን ጸሎት ቀናት፦ ጁን 7-15, 2023
ጁን 16, 2023፦ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ክብረ በዓል

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

ለዓመቱ መደበኛ ዘመን የመጽሐፍ ቅዱስ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ከላይ የቀረቡት ምስሎች፦ የተራራው ስብከት፣ በ ፍራ አንጀሊኮ፣ በ ዊኪሚዲያ ኮመንስ በኩል