አማርኛ

አስደንጋጭ ተቃርኖ! – የሆሣዕና እሑድ

እሑድ፣ ኤፕሪል 14፣ 2019

የጌታ ሕማማት የሆሣዕና እሑድ

የዛሬ ንባባት

የዛሬ ቅዱሳን ሁሉ

“ሆሣዕና! በጌታ ስም የሚመጣው የተባረከ ነው! የሚመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከ ነው! ሆሣዕና በአርያም!” ማርቆስ 11:9

በዛሬው ቅዳሴ እጅግ የሚቃረኑ ክስተቶችና ስሜቶች ያጋጥሙናል።  ኢየሱስ በታላቅ ደስታና እልልታ ወደ ኢየሩሳሌም እንዴት እንደተቀበለ የሚተርከውን በማዳመጥ ክብረ በዓላችንን እንጀምራለን!  “ሆሣዕና!” እያሉ ጮኹ።  “ሆሣዕና በአርያም!”  ኢየሱስ ሊደረግለት የሚገባው አቀባበል ተደረገለት።  ሰዎች እርሱን በማየታቸው ተደሰቱ፤ ታላቅ የደስታ ስሜትም ነበር። 

ነገር ግን የዛሬዎቹን ንባቦች በጥልቀት እየተከታተልን ስንሄድ፣ ይህ ደስታ በፍጥነት ወደ ድንጋጤና ሽብር ተለወጠ። ወንጌሉ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ “ኤሎኢ፣ ኤሎኢ፣ ለማ ሰባቅታኒ?” ማለትም፣ “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውኸኝ?” ብሎ በመጮኹ ወደ መደምደሚያው ይደርሳል። ከዚያም፣ “ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ነፍሱን ሰጠ።” በዚያን ጊዜ፣ የክርስቶስን ሞት እውነታ ስናሰላስል፣ መላው ምእመናን በዝምታ ይንበረከካሉ።

በአንድ አጭር ሳምንት ውስጥ ነገሮች እንዴት ሊለወጡ ይችላሉ! ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ እየጮኹ ያመሰግኑት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ምን ሆኑ? ለዚህ የመስቀል ስቃይና ሞት እንዲዳረግ እንዴት ሊፈቅዱ ቻሉ?

ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው ከሁሉ ጥልቅ የሆነ መልስ ያልጠበቅነው ሊሆን ይችላል።  መልሱም አብ ይህን ፈቅዶታል የሚል ነው።  አብ፣ ነገሮች እንዲከሰቱ በሚፈቅድበት ፈቃዱ፣ ብዙዎች በኢየሱስ ላይ እንዲነሡ፣ እንዲተዉትና እንዲሰቀል እንዲፈቅዱ ወደደ።  ይህን መረዳት እጅግ አስፈላጊ ነው። 

በዚያ የመጀመሪያው ቅዱስ ሳምንት በማንኛውም ጊዜ፣ ኢየሱስ መለኮታዊ ኃይሉን ተጠቅሞ መስቀሉን ለመቀበል እምቢ ማለት ይችል ነበር። ነገር ግን ይህን አላደረገም። ከዚህ ይልቅ፣ የሚደርስበትን ስቃይና መናቅ አስቀድሞ እያወቀና እየተቀበለ፣ ይህን ሳምንት በፈቃዱ አሳለፈ። ይህንም በግድ ወይም በጸጸት አላደረገውም። ይህን ሳምንት የራሱ ፈቃድ አድርጎ በመምረጥ፣ በፈቃደኝነት ተቀበለው።

እንዲህ ያለ ነገር ለምን ያደርጋል? ስቃይንና ሞትን ለምን ይመርጣል? ምክንያቱም፣ በአብ ፍጹም ጥበብ፣ ይህ ስቃይና ሞት ለታላቅ ዓላማ የሚውል ነበር። እግዚአብሔር የራሱን ስቃይና ስቅለት እኛን ወደ ቅድስና የሚያደርስ ፍጹም መንገድ በማድረግ፣ የዓለምን ጥበብ ለማሳፈር መረጠ። በዚህ ተግባር ከሁሉ የከፋውን ክፋት ከሁሉ ወደሚበልጠው መልካም ነገር ለወጠው። አሁንም፣ በዚህ ተግባር ላይ ካለን እምነት የተነሣ፣ የተሰቀለው ክርስቶስ ምስል ያለበት መስቀል በቤተ ክርስቲያኖቻችንና በቤቶቻችን ማዕከላዊ ቦታ ላይ ተሰቅሎ ይገኛል። ይህም ከሁሉ የከፋው ክፋት እንኳን የእግዚአብሔርን ኃይል፣ ጥበብና ፍቅር ሊያሸንፍ እንደማይችል ሁልጊዜ ያስታውሰናል። እግዚአብሔር ከሞት ራሱ ይልቅ ኃያል ነው፤ ሁሉም ነገር የጠፋ ቢመስልም እንኳን፣ የመጨረሻው ድል የእግዚአብሔር ነው።

ይህ ሳምንት ከእግዚአብሔር የሚመጣ ተስፋ እንዲሰጥህ ፍቀድ። ብዙ ጊዜ ለመደበት፣ ከዚያም የከፋው ደግሞ ተስፋ ለመቁረጥ ልንፈተን እንችላለን። ለእኛም ቢሆን ግን ሁሉም ነገር አልጠፋም። እኛ ካልፈቀድን በስተቀር፣ በመጨረሻ ደስታችንን ሊነጥቀን የሚችል ምንም ነገር የለም። ክርስቶስ ኢየሱስ የራሱን መስቀል በክብር በመቀበሉ፣ በሕይወታችን የምንታገሣቸውን ሁሉ እንዲለውጥ እየፈቀድንለት በእርሱ ጸንተን ከቆየን፣ ምንም ችግር፣ ምንም ሸክም፣ ምንም መስቀል ሊያሸንፈን አይችልም።

ዛሬ፣ ከሆሣዕና እሑድ እስከ ዓርብ ስቅለት ድረስ ስላለው የስሜቶች ተቃርኖ አሰላስል። ብዙዎች ኢየሱስ ሲገደል ባዩ ጊዜ ሊሰማቸው ስለነበረው ፍርሃት፣ ግራ መጋባትና ተስፋ መቁረጥ አስብ። እንዲሁም፣ አብ ይህን ከባድ ስቃይ ከታወቀው ሁሉ ለሚበልጠው መልካም ነገር ለማዋል ሲል የፈቀደበት መለኮታዊ ተግባር መሆኑን አሰላስል። ጌታ ሕይወቱን በፈቃዱ ሰጠ፤ አንተንም እንዲሁ እንድታደርግ ይጠራሃል። በሕይወትህ ያለውን መስቀል አሰላስል። በፈቃደኝነት እንደሚቀርብ መሥዋዕት ለእርሱ እያቀረብኸው፣ በነፃ ፈቃድህ ስትቀበለው፣ ጌታ ከዚህ የተትረፈረፈ ምሕረት በማፍለቅ ለመልካም ነገር ሊጠቀምበት እንደሚችል እወቅ። የተባረከ ቅዱስ ሳምንት ይሁንልህ! ዓይኖችህን በጌታ መስቀል እንዲሁም በራስህ መስቀል ላይ አድርግ።

ጌታ ሆይ፣ ተስፋ ለመቁረጥ ስፈተን ተስፋን ስጠኝ።  በነገር ሁሉ፣ እጅግ በሚያስጨንቁኝ ነገሮች ውስጥም እንኳ፣ መገኘትህን እንዳይ እርዳኝ።  አምላኬ ሆይ፣ ሁሉን ለአንተ አሳልፌ ስሰጥ፣ ይህ የሕማማት ሳምንት እጅግ ጨለማ የሆኑ ጊዜያቶቼንና ድካሜን ይለውጥ።  ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

40 ቀናት በመስቀሉ ሥር – ሠላሳ ዘጠነኛ ማሰላሰያ – የልጇን አስከሬን የታቀፈችው ማርያም

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

ለዐቢይ ጾም ተጨማሪ ንባቦች

ተጨማሪ ንባብ – የጌታ ሕማማት የሆሣዕና እሑድ