አማርኛ

ፍቅር በጥቃቅን ነገሮች ውስጥ ነው

ጁን 10፣ 2020
በዓመቱ ተራ ዘመን የአሥረኛው ሳምንት ረቡዕ
የዛሬ ንባቦች

“እውነት እላችኋለሁ፤ ሰማይና ምድር እስኪያልፉ ድረስ፣ ሁሉም እስኪፈጸም ድረስ፣ ከሕግ ከሁሉ ትንሹ ፊደል ወይም ከፊደል ከሁሉ ትንሹ ክፍል እንኳ አያልፍም።” ማቴዎስ 5:18

ይህ ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ ትኩረት የሚስብ ነው። ስለ ሕግና ኢየሱስ ሕግን ወደ ፍጻሜ ስለ ማድረሱ፣ ከዚህ አባባል ተነሥቶ ብዙ ነገር ሊባል ይችላል። ነገር ግን ልናሰላስለው የሚገባ አንድ ነገር አለ፤ ኢየሱስ የሕጉ አንድ ፊደል ብቻ ሳይሆን፣ በይበልጥም የፊደል ከሁሉ ትንሹ ክፍል እንኳ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየት ያደረገው ከፍተኛ ጥረት ነው።

በክርስቶስ ኢየሱስ ፍጻሜ ያገኘው የእግዚአብሔር ከሁሉ የላቀው ሕግ ፍቅር ነው። “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም አእምሮህ፣ በፍጹም ነፍስህና በፍጹም ኃይልህ ውደድ።” እንዲሁም፣ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።” ይህ የእግዚአብሔር ሕግ ፍጹም ፍጻሜ ነው።

ከላይ ያለውን ክፍል ከፍቅር ሕግ ፍጹምነት አንጻር ከተመለከትነው፣ ኢየሱስ የፍቅር ጥቃቅን ነገሮች፣ እንዲያውም ከሁሉ የሚያንሰው ዝርዝር እንኳ፣ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ሲናገር መስማት እንችላለን። በእርግጥም ፍቅርን በእጥፍ ድርብ እንዲያድግ የሚያደርጉት እነዚህ ጥቃቅን ነገሮች ናቸው። አንድ ሰው እግዚአብሔርንና ባልንጀራውን በመውደድ ውስጥ ትኩረት የሚሰጠው ነገር ጥቃቅን እየሆነ በሄደ መጠን፣ የፍቅር ሕግን እስከ ከፍተኛው ደረጃ መፈጸሙም እየበለጠ ይሄዳል።

ዛሬ፣ እንድትወዳቸው እግዚአብሔር በሕይወትህ ውስጥ ስላስቀመጣቸው ሰዎች አስብ። ይህ በተለይ የሚመለከተው የቤተሰብ አባላትን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ባልና ሚስትን ነው። ለእያንዳንዱ ትንሽ የደግነትና የርኅራኄ ተግባር ምን ያህል ትኩረት ትሰጣለህ? የሚያበረታታ ቃል ለመናገር ዕድሎችን በየጊዜው ትፈልጋለህ? ከሁሉ በሚያንሱ ነገሮች እንኳ፣ እንደምታስብላቸው፣ ከጎናቸው እንዳለህና ስለ እነርሱ እንደሚያሳስብህ ለማሳየት ትጥራለህ? ፍቅር በጥቃቅን ነገሮች ውስጥ ነው፤ እነዚህም ጥቃቅን ነገሮች ይህን ክቡር የእግዚአብሔር የፍቅር ሕግ ፍጻሜ ያጎላሉ።

ጌታ ሆይ፣ አንተንና ሌሎችን እንድወድ የተጠራሁባቸውን ትልልቅና ብዙ ጥቃቅን መንገዶች ሁሉ በትኩረት እንዳይ እርዳኝ። በተለይም ይህን ፍቅር ለማሳየት ከሁሉ የሚያንሱትን ዕድሎች እንኳ እንድፈልግና በዚህም ሕግህን እንድፈጽም እርዳኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ የዘጠኝ ቀን ጸሎት
የዘጠኝ ቀን ጸሎቱ ቀናት፦ ጁን 10-18, 2020
ጁን 19, 2020፦ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ታላቅ በዓል

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ሥዕል፦ ሁሉን የሚገዛው ክርስቶስ