አማርኛ

ተሸክመን ወደ ቤት መድረስ

ኖቬምበር 4, 2021
በዓመቱ የተለመደ ዘመን ሠላሳ አንደኛ ሳምንት ሐሙስ
የዛሬ ንባቦች

ቅዱስ ቻርልስ ቦሮሜዎ፣ ጳጳስ—መታሰቢያ

ቪዲዮ

“ከእናንተ መካከል መቶ በጎች ያሉት፣ ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋበት፣ ዘጠና ዘጠኙን በምድረ በዳ ትቶ፣ የጠፋውን እስኪያገኘው ድረስ ፍለጋ የማይሄድ ማን አለ? ባገኘውም ጊዜ በታላቅ ደስታ በትከሻው ይሸከመዋል፤ ወደ ቤቱም ሲደርስ ወዳጆቹንና ጎረቤቶቹን ሰብስቦ፣ ‘የጠፋውን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ’ ይላቸዋል።”  ሉቃስ 15:4–6

ከታላላቅ ቅዱሳን አንዳንዶቹ መቶ የሚለው ቁጥር ፍጹምነትን እንደሚወክል ያመለክታሉ። መቶ የሚለው ቁጥር የሚያመለክተው በሰማይ ያሉትን ቅዱሳን ሁሉ ብቻ ሳይሆን መላእክትንም የሚያካትተውን የእግዚአብሔር መንግሥት ፍጹምነት ነው። ያ አንድ የጠፋ በግ በዚህ ሕይወት ጉዞ ላይ ያለነውን የሰው ልጆች ሁሉ ይወክላል። ኢየሱስ ደግሞ ትኩረቱን ወደ ወደቀው የሰው ዘር የሚያዞር፣ ተሸክሞ ወደ ቤት ሊያደርሰንም በትጋት የሚፈልገን እረኛ ነው።

በመጀመሪያ፣ እረኛው ያን አንድ የተቅበዘበዘ በግ የሚፈልገው ከቁጣ የተነሣ ሳይሆን ከአሳቢነትና ከፍቅር የተነሣ መሆኑን ልብ በሉ። ስንቅበዘበዝ ጌታችን እንዴት እንደሚያየን በትክክል ለመረዳት፣ ይህን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። ለእኛ ያለውን ጥልቅ አሳቢነት፣ እኛን ለመፈለግ የሚያደርገውን ትጋት፣ እንዲሁም በመቅበዝበዝ ውስጥ ሳለን እኛን ለማግኘት ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት ማየት አለብን። ይህ ከሩቅ ተቀምጦ በፍርድና በቁጣ የሚመለከተን አምላክ አይደለም፤ ይልቁንም እኛን አግኝቶ ወደ ቤት ለማምጣት ወደ እኛ የመጣ፣ የወደቀውን የሰው ተፈጥሮአችንን የተዋሐደ፣ መከራንም ሁሉ የታገሠ አምላክ ነው።

በዚህ ምሳሌ ውስጥ እረኛው የጠፋውን በግ በትከሻው አስቀምጦ ወደ ቤት እንደሚሸከመውም ልብ በሉ። ብዙ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያለብን በራሳችን ጥረት ብቻ እንደሆነ በማሰብ ወጥመድ ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን። እውነቱ ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ በዚያው ሆኖ፣ አንሥቶ ሊሸከመንና ወደ ቤት ሊያደርሰን እየጠበቀን መሆኑ ነው። የእኛ ድርሻ ራሳችንን ለመሐሪ እጆቹ መስጠትና መሸሻችንን ማቆም ነው። ይህም ወደ እርሱ በመዞር፣ ወደ እኛ እንዲመጣና እንዲያገለግለን በመፍቀድ ይሆናል። አንዴ ራሳችንን በርኅራኄ ለሚዳስሱ እጆቹ ከሰጠን በኋላ፣ ዋነኛውን ጥረት የሚያደርገው ጌታችን ነው።

በመጨረሻም፣ በዚህ ምሳሌ ውስጥ የተጠቀሰው ደስታ የእረኛው መሆኑን ልብ በሉ። እርግጥ ነው፣ ተነሥተንና ተሸክመን ፍጹም ወደሆነው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ቤታችን ስንደርስ እኛም ደስ ይለናል፤ የእኛ ደስታ ግን ለጌታችን ደስታ የምንሰጠው ምላሽ ነው። እንድንካፈል የተጋበዝነው በእርሱ ደስታ ነው። በርኅራኄ ተሸክሞ ወደ ቤት እንዲያደርሰን ስንፈቅድለት፣ በምስጋና የሚሞላው የእርሱ ልብ ነው። “የጠፋውን በጌን አግኝቻለሁና ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ” ይላል።

ዛሬ፣ ስለዚህ ስለ መልካሙ እረኛ ቅዱስ ምስል አሰላስሉ። ይህን ምሳሌና የሚያሳየውን ምስል ስታሰላስሉ፣ በውስጣችሁ ለሚነሡት የተለያዩ ሐሳቦች፣ ትዝታዎች፣ ስሜቶችና ፍርሃቶች ትኩረት ስጡ። እያንዳንዳችን የተለያየን ነን፤ ጌታችንም ወደ እያንዳንዳችን፣ በኃጢአታችን መካከል ወዳለንበት ቦታ እንዳለን ሊመጣ እጅግ ይፈልጋል። የዚህን መልካም እረኛ ርኅራኄ ማሰላሰል፣ ጌታችን እንዲናገራችሁና እያንዳንዳችሁ ከተቅበዘበዛችሁባቸው መንገዶች ተመልሳችሁ ወደ እርሱ እንድትመጡ በግላችሁ እንዲጋብዛችሁ በሩን ይከፍታል። አትሽሹ። ወደ እናንተ ሲመጣ በመተማመን ጸንታችሁ ቆዩ። ድምፁን አዳምጡ፤ ተሸክሞ ወደ ቤት ሊያደርሳችሁ ሲያነሣችሁም “እሺ” በሉት።

የዋሁ ኢየሱሴ ሆይ፣ አንተ መልካሙ እረኛ ነህ። ትወደኛለህ፤ በትጋትና በታማኝነትም ትፈልገኛለህ። ከአንተ መሸሽንና ከለዘበ ድምፅህ መሰወርን እስካቆም ድረስ በአንተ ልታመን። እባክህ ወደ እኔ ና፣ አንሣኝ፣ በትከሻህ ላይ አስቀምጠህም ወደ ቤት ተሸከመኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

ሁሉም ቅዱሳን/በዓላት

የዕለቱ ቅዱስ – ቅዱስ ቻርልስ ቦሮሜዎ፣ ጳጳስ

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ከላይ የቀረበው ምስል፦ በሚርያምስ-ፎቶስ፣ ከፒክሳቤይ