ኦክቶበር 29፣ 2020
በዓመቱ ተራ ዘመን የሠላሳኛው ሳምንት ሐሙስ
የዛሬ ንባቦች

አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ መጥተው፣ “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ውጣ፤ ይህን አካባቢ ለቅቀህ ሂድ” አሉት። እርሱም፣ “ሂዱና ያን ቀበሮ፣ ‘እነሆ፣ ዛሬና ነገ አጋንንትን አወጣለሁ፣ ድውያንንም እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛውም ቀን ዓላማዬን እፈጽማለሁ’ በሉት” ብሎ መለሰላቸው። ሉቃስ 13:31-32
በኢየሱስና በአንዳንድ ፈሪሳውያን መካከል የተደረገው ይህ ውይይት ምንኛ ትኩረትን የሚስብ ነበር! የፈሪሳውያንንም ሆነ የኢየሱስን ድርጊት መመልከት ትኩረትን ይስባል።
ፈሪሳውያን የሄሮድስን ዓላማ እያስጠነቀቁ፣ ለምን ኢየሱስን በዚህ መንገድ እንዳነጋገሩት መጠየቅ ይቻላል። ለኢየሱስ ተጨንቀው ሊረዱት ነበርን? ምናልባት እንዲያ አልነበረም። ይልቁንም፣ አብዛኞቹ ፈሪሳውያን በኢየሱስ እንደሚቀኑና እንደሚመቀኙበት እናውቃለን። በዚህ ጊዜ፣ ስለ ሄሮድስ ቁጣ ያስጠነቀቁት፣ እርሱን በማስፈራራት ከአካባቢያቸው እንዲወጣ ለማድረግ የሞከሩበት መንገድ ይመስላል። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ አልተሸበረም።
አንዳንድ ጊዜ እኛም ተመሳሳይ ነገር ያጋጥመናል። አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው ሊረዳን የሚሞክር መስሎ፣ ስለ እኛ የተወራ ሐሜት መጥቶ ሊነግረን ይችላል፤ በእውነቱ ግን ይህ በፍርሃት ወይም በጭንቀት ሊሞላን የሚሞክርበት ስውር የማስፈራሪያ መንገድ ነው።
ዋናው ነገር፣ ሞኝነትና ክፋት ሲገጥሙን፣ ኢየሱስ በሰጠው መልስ ዓይነት ብቻ ምላሽ መስጠት ነው። ኢየሱስ ለማስፈራሪያው አልተንበረከከም። የሄሮድስ ክፋት ፈጽሞ አላስጨነቀውም። ከዚህ ይልቅ፣ ለፈሪሳውያን በሰጠው መልስ፣ በአንድ አነጋገር፣ “በፍርሃት ወይም በጭንቀት ልትሞሉኝ እየሞከራችሁ ጊዜያችሁን አታጥፉ። የአባቴን ሥራዎች እየሠራሁ ነው፤ ሊያሳስበኝ የሚገባውም ይህ ብቻ ነው” እንዳላቸው ነበር።
በሕይወትህ የሚረብሽህ ምንድን ነው? የሚያስፈራራህስ ምንድን ነው? የሌሎች ሰዎች አስተያየት፣ ክፋት ወይም ሐሜት ተስፋ እንዲያስቆርጥህ ትፈቅዳለህን? ሊያሳስበን የሚገባው ብቸኛው ነገር የሰማዩን አባት ፈቃድ ማድረግ ነው። ፈቃዱን በመተማመን ስንፈጽም፣ በሕይወታችን ያሉትን ማታለያዎችና ከንቱ ማስፈራሪያዎች ሁሉ ለመቃወም የሚያስፈልገንን ጥበብና ድፍረትም እናገኛለን።
ዛሬ፣ በሕይወትህ የአብን ፈቃድ ለመፈጸም ባለህ ቁርጠኝነት ላይ አሰላስል። ፈቃዱን እየፈጸምህ ነውን? እንዲህ ከሆነ፣ አንዳንድ ሰዎች መጥተው ከዚህ ሊያግዱህ ሲሞክሩ ታያለህን? እንደ ኢየሱስ ያለ መተማመን እንዲኖርህ ጣር፤ ትኩረትህንም እግዚአብሔር በሰጠህ ተልእኮ ላይ አድርግ።
ጌታ ሆይ፣ በመለኮታዊ ፈቃድህ በእውነት እታመናለሁ። ለእኔ ባዘጋጀኸው ዕቅድ እታመናለሁ፤ በሌሎች ሰዎች ሞኝነትና ክፋት ለመወሰድም ሆነ ለመሸበር ፈቃደኛ አይደለሁም። በሁሉም ነገር ዓይኖቼን ወደ አንተ አድርጌ እንድኖር ድፍረትንና ጥበብን ስጠኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
ለአሜሪካ ምርጫዎች የሚሆኑ ጸሎቶች & አጋዥ ግብዓቶች




