አማርኛ

ጠይቁ፣ መልካም ነገሮችም ሁሉ ይሰጧችኋል

ማርች 5, 2020
የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት ሐሙስ
የዛሬ ንባባት

“ጠይቁ፣ ይሰጣችኋል፤ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ፣ በሩም ይከፈትላችኋል…”

“እንግዲያስ የሰማዩ አባታችሁ ለሚጠይቁት መልካም ነገሮችን እንዴት አብልጦ አይሰጥ!”  ማቴዎስ 7:7, 11

ኢየሱስ፣ ስንጠይቅ እንደምንቀበል፣ ስንፈልግ እንደምናገኝ፣ ስናንኳኳም በሩ እንደሚከፈትልን በግልጽ ይናገራል።  ነገር ግን የአንተ ተሞክሮ ይህን ይመስላል?  አንዳንድ ጊዜ ደጋግመን ልንጠይቅና ልንማጸን እንችላለን፤ ጸሎታችን ግን መልስ ያላገኘ ይመስለናል፤ ቢያንስ እኛ በምንፈልገው መንገድ መልስ ያላገኘ ይመስለናል።  ታዲያ ኢየሱስ “ጠይቁ…ፈልጉ…አንኳኩ” እናም ትቀበላላችሁ ሲል ምን ማለቱ ነው?

ይህን የጌታችንን ማበረታቻ ለመረዳት ቁልፉ፣ ከላይ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደሚገልጸው፣ በጸሎታችን አማካይነት እግዚአብሔር ለሚጠይቁት “መልካም ነገሮችን” እንደሚሰጥ ማወቅ ነው።  የጠየቅነውን ሁሉ እንደሚሰጠን ቃል አይገባልንም፤ ይልቁንም በእውነት መልካም የሆነውን፣ በተለይም ለዘላለማዊ ድኅነታችን መልካም የሆነውን እንደሚሰጠን ቃል ይገባልናል።

ይህም “ታዲያ እንዴት ልጸልይ? ስለ ምንስ ልጸልይ?” የሚለውን ጥያቄ ያስነሣል።  በእርግጥ፣ የምናቀርበው እያንዳንዱ የልመና ጸሎት የጌታ ፈቃድ እንዲፈጸም የሚጠይቅ ሊሆን ይገባል፤ ከዚያ የሚበልጥም ሆነ የሚያንስ ምንም ነገር ሳንጠይቅ።  ፍጹም የሆነውን ፈቃዱን ብቻ።

ለዚህ መጸለይ መጀመሪያ ከምናስበው ይልቅ ከባድ ሊሆን ይችላል።  ብዙ ጊዜ “የአንተ ፈቃድ ይሁን” ከማለት ይልቅ “የእኔ ፈቃድ ይሁን” ብለን ወደ መጸለይ እናዘነብላለን።  ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ ፍጹም እንደሆነና “መልካም ነገሮችን” ሁሉ እንደሚያስገኝልን በጥልቅ ከታመንን፣ ፈቃዱን መፈለግ፣ እርሱንም መለመንና የልቡን በር ማንኳኳት፣ እግዚአብሔር ሊሰጠን እንደሚፈልገው የጸጋ ብዛትን ያስገኝልናል።

ዛሬ፣ የምትጸልይበትን መንገድ አስብበት።  ጸሎትህ፣ አንተ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ የምትፈልጋቸውን ብዙ ነገሮች ከመሻት ይልቅ፣ እግዚአብሔር ሊሰጥህ የሚፈልጋቸውን መልካም ነገሮች የሚሻ እንዲሆን ለመለወጥ ሞክር።  መጀመሪያ ከራስህ ሐሳብና ፈቃድ መላቀቅ ከባድ ሊሆንብህ ይችላል፤ በመጨረሻ ግን ከእግዚአብሔር በሚመጡ ብዙ መልካም ነገሮች ትባረካለህ።

ጌታ ሆይ፣ በሁሉም ነገር ፈቃድህ እንዲፈጸም ከልቤ እጸልያለሁ።  ከሁሉ በላይ ራሴን ለአንተ ለመስጠትና በፍጹም ዕቅድህ ለመታመን እሻለሁ።  ውድ ጌታ ሆይ፣ የራሴን ሐሳቦችና ምኞቶች ትቼ ፈቃድህን ሁልጊዜ እንድፈልግ እርዳኝ።  ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

40 ቀናት ከመስቀሉ ሥር – ስምንተኛ ማሰላሰል – በሁሉም ነገር ታማኝ መሆን

ለዐቢይ ጾም የሚረዱ ግብዓቶች

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች