አማርኛ

ስደት

ሜይ 16፣ 2020
የትንሣኤ አምስተኛ ሳምንት ቅዳሜ
የዛሬ ንባቦች

“‘ባሪያ ከጌታው አይበልጥም’ ብዬ የነገርኋችሁን ቃል አስታውሱ። እኔን ካሳደዱ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል።”  ዮሐንስ 15:20

እንደ ኢየሱስ መሆን ትፈልጋላችሁ?  ከሆነ፣ ይህ ምን ማለት እንደሆነ በጥንቃቄ አስቡ።  ወደ ክርስቶስ ይበልጥ በቀረብን መጠን፣ ዓለም ይበልጥ ይወደናል፣ ይረዳናልም ብሎ ማሰብ ቀላል ነው።  ሁሉም ሰው ቅድስናችንን አይቶ ያደንቃል፣ በሕይወታችንም ሁሉ መልካምና ቀላል ይሆናል ብለን ልናስብ እንችላለን።

ነገር ግን እንዲህ እንዳልሆነ ለማወቅ፣ የክርስቶስን ሕይወት መመልከት ብቻ ይበቃናል።  እርሱ በሁሉም ረገድ ፍጹም እንደነበረ ግልጽ ነው።  በዚህም ምክንያት፣ በእጅጉ ተንኮልና ስደት ተፈጸመበት።  በእርግጥ እስከ መግደል መድረሳቸውን፣ ይህን አስፈሪ እውነታ፣ መረዳት አዳጋች ነው።  በሌሊት ጨለማ ተያዘ፣ ለይስሙላ ችሎት ቀረበ፣ ጥፋተኛ ተብሎም የሞት ፍርድ ተፈረደበት።  ከዚያም ቅጣቱ ወዲያውኑ ተፈጸመ።

ይህን በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ለምን አደረጉ?  በሁሉም ረገድ እንዲህ ፍጹምና መሐሪ የሆነው ለምን እንዲህ ባለ ጭካኔ ይንገላታል?  

እንደ መጀመሪያዎቹ ተከታዮቹ በዚያ ብንኖር ኖሮ፣ ምናልባትም በጣም ደንግጠን፣ ፈርተን፣ ተሰናክለንና ግራ ተጋብተን ይሆን ነበር።  ኢየሱስ ነገሩን አበላሸው ብለን አስበን፣ በእርሱ ያለንን ተስፋ አጥተን ሊሆን ይችል ነበር።  ነገር ግን ዕቅዱ በሁሉም ረገድ ፍጹም ነበር፤ የሐሰት ክሶችንና በተንኮል የሚፈጸምበትን ስደት መታገሡም በዕቅዱ ውስጥ ዋና ቦታ ነበረው።  ይህን ግፍ በፈቃዱ በመቀበልም ዓለምን ተቤዠ።

ስለዚህ፣ “እንደ ኢየሱስ መሆን ትፈልጋላችሁ?” ወደሚለው የመጀመሪያ ጥያቄ እንመለስ።  በእርሱ ላይ የደረሰውን ከግምት አስገብተን ስንመለከተው፣ ይህ ከባድ ጥያቄ ነው።  “ባሪያ ከጌታው አይበልጥም።”  “እኔን ካሳደዱ፣ እናንተንም ያሳድዷችኋል።”  እነዚህ ለመቀበልና እሺ ለማለት የሚከብዱ ቃላት ናቸው።  

ስደት ልንሸሸው የሚገባ ነገር አይደለም።  ቢደርስብን ተስፋ ልንቆርጥ ወይም ራሳችንን ዝቅ ልናደርግ አይገባም።  ለምን?  ምክንያቱም ስደት የጌታችንን ፈለግ እየተከተልን መሆናችን ግልጽ ምልክት ነው።  በስደት ምክንያት፣ እኛ ልንገነዘበው ከምንችለው እጅግ በላይ ከክርስቶስ ጋር በጥልቅ እንዋሐዳለን። 

ዋናው ነገር፣ እኛ ከፈቀድንለት፣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ የሚደርሰውን ግፍ ሁሉ ለበጎ ሊጠቀምበት እንዳሰበ ማወቅ ነው።  ይህንንም በእጁ ስናስረክብና እያጉረመረምን ሳይሆን በፈቃዳችን ስንቀበለው፣ ለበጎ እንዲጠቀምበት እንፈቅድለታለን።  አምላካችን የሆነውን ጌታችንን ፈለግ ለመከተል ብቁ ሆነን ስለተገኘን፣ ምላሻችን “ደስ መሰኘትና ሐሴት ማድረግ” መሆን አለበት።

በእምነታችሁና ወንጌልን በመቀበላችሁ ምክንያት ስለሚደርስባችሁ ማንኛውም ዓይነት ስደት ወይም ግፍ ዛሬ አሰላስሉ።  ጌታ ከፈቀዳችሁለት ይህን ሊጠቀምበት ይፈልጋል።

ጌታ ሆይ፣ የሚያከብድብኝን ሁሉ በእጅህ አስረክባለሁ።  ተከታይህ በመሆኔ የሚደርስብኝን ማንኛውንም መከራ ለአንተ እሰጣለሁ።  በመከራህ ብቻ ሳይሆን፣ መከራን በፈቃድህ በመቀበልህም አንተን ልምሰል።  ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ምስል፦ የክርስቶስ መገረፍ፣ በኒኮላ ግራሲ



በመስቀሉ ሥር 40 ቀናት፦
ከብፅዕት እናታችን ልብ የሚመነጭ የፍቅር እይታ