ዲሴምበር 28፣ 2019
ቅዱሳን ንጹሐን ሕፃናት ሰማዕታት—በዓል
የገና በዓል ስምንት ቀናት አራተኛ ቀን
የዛሬ ንባባት

ሄሮድስ ሰብአ ሰገል እንዳታለሉት ባወቀ ጊዜ እጅግ ተቆጣ። ከሰብአ ሰገል በጥንቃቄ ባጣራው ጊዜ መሠረት፣ በቤተ ልሔምና በዙሪያዋ ያሉት ዕድሜያቸው ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑ ወንድ ሕፃናት ሁሉ እንዲጨፈጨፉ አዘዘ። ማቴዎስ 2:16
ዛሬ፣ በገና በዓል ስምንት ቀናት አራተኛው ቀን፣ በዲሴምበር 26፣ በቅዱስ እስጢፋኖስ ሰማዕትነት በዓል ከተሰጠን ጋር የሚመሳሰል ምስክርነት ተሰጥቶናል። የዛሬው በዓል ግን ያንኑ ክፋት በተለየና ይበልጥ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ያሳየናል። እዚህ፣ ሄሮድስ በቅናትና በጥላቻ ተነሣሥቶ፣ አዲስ የተወለደውን ንጉሥ ኢየሱስን ለማጥፋት በማሰብ፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ንጹሐን ሕፃናት አስገደለ።
ወታደሮቹ እየተዘዋወሩ እነዚያን ንጹሐን ሕፃናት ሲገድሉ፣ ወላጆቻቸውም ምንም ማድረግ አቅቷቸው ሲመለከቱ፣ የቤተ ልሔምን ከተማና አካባቢዋን ሞልቶት የነበረውን ሐዘን በእሳብ ለመገመት ብቻ ነው የምንችለው። በአንድ በኩል፣ እግዚአብሔር ይህ እንዲሆን እንደፈቀደ ማወቅ ያስደነግጣል። በሌላ በኩል ግን፣ በጥልቅ እምነት፣ እነዚህ ንጹሐን ሕፃናት የሰጡትን ምስክርነት ለመረዳት መጣር አለብን።
ይህ በቃላት ሊገለጽ የማይችል ወንጀልና ክፋት ቢሆንም፣ ከዘላለም አንጻር ሲታይ፣ እግዚአብሔር ፍትሕ ይሰጥበታል። እነዚህ ንጹሐን ሰለባዎች በሰማይ ለዘላለም የሰማዕትነት አክሊል ይደፋሉ፤ አዲስ ለተወለደው ንጉሥ የመጀመሪያዎቹ ምስክሮች በመሆናቸውም በመላእክትና በቅዱሳን ይከበራሉ። ይህ በዚያን ጊዜ ሥቃዩን ያስታገሰ ባይሆንም፣ እነዚያ ቤተሰቦች ፍትሕ ወደ ሰፈነበት ሰማይ ሲገቡ፣ የተሰማቸውን ሥቃይ በእርግጥ ይለውጠዋል።
ምስክርነታቸው ስለ ራሳችን ሕይወት ብዙ ነገር ይገልጥልናል። በሕይወት ውስጥ ነገሮች ቅንነትና ፍትሕ የጎደላቸው የሚሆኑባቸው ብዙ ጊዜያት እንዳሉ ያሳየናል። የእነዚህ ንጹሐን ሕፃናት እልቂት ይህን እውነታ አጥብቆ ያስታውሰናል። ሆኖም አጥብቀን ልንይዘው የሚገባን አንድ ነገር አለ፤ እግዚአብሔር በመጨረሻ እያንዳንዱን በደል ያስተካክላል። ዛሬ እነዚህን ሕፃናት ለማክበር ታላቅ በዓል እናከብራለን፤ ይህም እግዚአብሔር ይህን አሳዛኝ ክስተት ወደ ክብር እንደለወጠው የምንመሰክርበት መንገድ ነው።
ለእያንዳንዳችንም እንዲሁ ነው። ያንተም «አሳዛኝ ክስተት» ምንም ይሁን ምን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ሁሉን ነገር ወደ ትክክለኛ ሁኔታ ለመመለስ የወደቀውን የሰው ተፈጥሮአችንን ተቀብሎ ወደ ዓለማችን እንደገባ ዕወቅ።
ዛሬ፣ በዚህ የገና ዘመን ከሁሉ ይበልጥ ስለሚያሠቃይህ ነገር አሰላስል። ምንም ይሁን ምን፣ ዛሬ ቁስልህንና ሥቃይህን እነዚህን ታናናሽ ሕፃናት ካጡት ቤተሰቦች ሐዘን ጋር እንድታዋሕድ ተጋብዘሃል። እግዚአብሔር በመጨረሻ ለእነርሱ ሁሉ ያደረገውን ለአንተም እንዲያደርግ ፍቀድለት። ሰው መሆኑ፣ ሞቱና ትንሣኤው ቁስልህን ወደ ሰማዕትነት አክሊል እንዲለውጡት ፍቀድ። በመጨረሻ፣ ከፈቀድክለት፣ ጌታ በሕይወትህ ድል አድራጊ ይሆናል።
ጌታ ሆይ፣ ቁስሌን፣ ሥቃዬንና ግራ መጋባቴን ሁሉ ለአንተ አስረክባለሁ። ዛሬ እነዚህን ታናናሽ ሕፃናት ካጡት ሰዎች ሐዘን ጋር ራሴን አዋሕዳለሁ፤ አሁን በሰማይ ከአንተ ጋር እየነገሡ ያሉት የእነዚህ ሕፃናት ሕይወት፣ ለወደፊቱ የሚሆነውን የሚያሳየኝ ምልክት እንደሆነ እታመናለሁ። በዓለማችን መወለድህ፣ አንተ መድኃኒታችን እንደሆንክና ሁሉንም ወደ መልካም መለወጥ እንደምትችል ከሁሉ የሚበልጠው ምልክት ነበር። ኢየሱስ ሆይ፣ ሕይወቴን በእምነት ለአንተ አስረክባለሁ፤ እያንዳንዱን በደል እንደምታስተካክልም አውቃለሁ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።
ይህንም ይመልከቱ – በጋራ የሚካፈሉት ሥቃይ




