አማርኛ

ጠላቶቻችሁን አፍቅሩ

ጁን 14, 2022
በዓመቱ መደበኛ ዘመን የአሥራ አንደኛው ሳምንት ማክሰኞ
የዛሬ ንባባት

ቪዲዮ

“እኔ ግን እላችኋለሁ፤ የሰማዩ አባታችሁ ልጆች እንድትሆኑ፣ ጠላቶቻችሁን አፍቅሩ፣ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ።” ማቴዎስ 5:44-45a

ይህ ከጌታችን የመጣ ቀላል ትእዛዝ አይደለም። ነገር ግን የፍቅር ትእዛዝ ነው።

በመጀመሪያ፣ ጠላቶቻችንን እንድናፈቅር ይጠራናል። ጠላቶቻችን እነማን ናቸው? ሆን ብለን ለመጥላት የመረጥናቸው ሰዎች በሚለው ትርጉም “ጠላቶች” እንደሌሉን ተስፋ እናደርጋለን። ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ በእነርሱ ላይ ለመቆጣት የምንፈተንባቸውና እነርሱን ለማፍቀር የሚከብደን ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ምናልባትም ከእርሱ ጋር ለመስማማት የምንቸገርበትን ማንኛውንም ሰው እንደ ጠላታችን ልንቆጥረው እንችላለን።

እነርሱን ማፍቀር ማለት የግድ የቅርብ ወዳጆቻቸው መሆን አለብን ማለት አይደለም። ነገር ግን እንክብካቤ፣ አሳቢነት፣ መረዳትና ይቅርታ ያለበት እውነተኛ የፍቅር ስሜት ለእነርሱ እንዲኖረን መጣር አለብን ማለት ነው። ለሁሉም ሰው እንዲህ ያለ ስሜት መያዝ ከባድ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ግባችን መሆን አለበት።

የዚህ ትእዛዝ ሁለተኛ ክፍል ይረዳናል። ለሚያሳድዱን መጸለይ፣ ልናዳብረው በሚገባን ተገቢ ፍቅርና መዋደድ እንድናድግ ይረዳናል። ይህ የፍቅር ገጽታ በጣም ከባድ ቢሆንም፣ ምን እንደሚጠይቅ ግን ግልጽ ነው።

ለማፍቀር በጣም የሚከብዷችሁን ሰዎች አስቡ። በእነርሱ ላይ ቁጣ የሚሰማችሁን አስቡ። የቤተሰብ አባል፣ የሥራ ባልደረባ፣ ጎረቤት ወይም ቀደም ሲል የምታውቁትና እስካሁን ያልታረቃችሁት ሰው ሊሆን ይችላል። በውጫዊ ግንኙነታችሁም ሆነ በውስጣችሁ፣ ከእርሱ ጋር ለመስማማት የምትቸገሩበት ቢያንስ አንድ ሰው፣ ወይም ምናልባት ከአንድ በላይ ሰዎች እንዳሉ በቅንነት መቀበል ከዚህ የወንጌል ክፍል ጋር ይስማማል። ይህን መቀበል በቀላሉ የቅንነት ተግባር ነው።

ይህን ሰው ወይም እነዚህን ሰዎች ከለያችሁ በኋላ፣ ለእነርሱ ትጸልዩ እንደሆነ አስቡ። በመደበኛነት ጊዜ ወስዳችሁ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር ታቀርቧቸዋላችሁ? እግዚአብሔር ጸጋውንና ምሕረቱን በእነርሱ ላይ እንዲያፈስ ትጸልያላችሁ? ይህን ማድረግ ሊከብድ ይችላል፤ ነገር ግን ለውስጣዊ ጤንነታችሁ እጅግ ከሚጠቅሙ ተግባሮች አንዱ ነው። ፍቅርንና መዋደድን ለእነርሱ ማሳየት ሊከብድ ይችላል፤ ለእነርሱ ለመጸለይ አስቦ መወሰን ግን አይከብድም።

ከእነርሱ ጋር ለመስማማት ለምንቸገርባቸው ሰዎች መጸለይ፣ እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ ለእነርሱ እውነተኛ ፍቅርና አሳቢነት እንዲያሳድግ ለመፍቀድ ቁልፍ ነው። ይህም የቁጣ ወይም የጥላቻ ስሜትን እንኳ ይዘን እንዳንቀጥል፣ እግዚአብሔር ስሜቶቻችንንና ውስጣዊ ምላሾቻችንን እንደ አዲስ እንዲቀርጽ የምንፈቅድበት መንገድ ነው።

ዛሬ፣ ከሁሉ በላይ ከእርሱ ጋር ለመስማማት ለምትቸገሩበት ሰው ለመጸለይ ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። ይህ ጸሎት ለእርሱ ያላችሁን ፍቅር በአንድ ሌሊት የመለወጡ ዕድል እጅግ አነስተኛ ነው። ነገር ግን በዚህ ዓይነት ጸሎት በየቀኑ ለመጽናት ከወሰናችሁ፣ ጊዜ እያለፈ ሲሄድ እግዚአብሔር ልባችሁን ቀስ በቀስ ይለውጣል። ለሁሉም ሰዎች እንዲኖራችሁ ከሚፈልገው ፍቅር ሊያግዳችሁ ከሚችል የቁጣና የተጎዳ ስሜት ሸክምም ነጻ ያወጣችኋል።

ፍጹም ፍቅር ያለህ ጌታ ሆይ፣ እንድጸልይለት ለምትፈልገው ሰው እጸልያለሁ። ሰዎችን ሁሉ እንድወድ፣ በተለይም ለመውደድ የሚከብዱትን እንድወድ እርዳኝ። ለእነርሱ ያለኝን ስሜት አስተካክል፣ ከማንኛውም ቁጣ ነፃ እንድሆንም እርዳኝ። ኢየሱስ ሆይ፣ በአንተ እታመናለሁ።

ለኢየሱስ ቅዱስ ልብ የሚቀርብ የዘጠኝ ቀን ጸሎት
የዘጠኝ ቀን ጸሎቱ ቀናት፦ ጁን 15-23, 2022
ጁን 24, 2022፦ የኢየሱስ ቅዱስ ልብ ታላቅ በዓል

ተጨማሪ የወንጌል ማሰላሰያዎች

በእግዚአብሔር ምሕረት ላይ ማሰላሰያዎች

የዛሬ ቅዱሳን/በዓላት

የቅዳሴ ንባብ አማራጮች

ከላይ የቀረበው ዋና ምስል፦ በሂየሮኒሙስ ቦሽ የተሣለው «የእሾህ አክሊል የተደፋበት ክርስቶስ»፣ ከዊኪፔዲያ የተገኘ